የሃዋሳ ከተማ ቀጣይ እጣ ፈንታ በአብሮነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለነዋሪዎች ሥጋት ሊሆን አይገባም.... አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ

101


ሀዋሳ ሚያዚያ 7 ቀን 2011ዓ.ም የሃዋሳ ከተማ ቀጣይ እጣ ፈንታ በአብሮነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በወቅታዊ ጉዳዮች የተፈጠረው ጫና ለነዋሪዎቿ ሥጋት ሊሆን አይገባም ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገለፁ ፡፡

የከተማዋ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮችና ታክስ አስተዳደር ላይ ከከተማዋ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ትናንት ተወያይቷል ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ከተማዋ አሁን ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ነዋሪዎቿና ግብር ከፋዩ የንግዱ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀጣይ የከተማዋ እጣ ፋንታም በነዋሪዎቿ አብሮነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልፀው የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ያለበትን ደረጃ ተከትሎ የሚፈጠሩ ጫናዎች ለከተማው ህዝብ ሥጋት ሊሆኑ እንደማይገባም አመልክተዋል ፡፡

ጥያቄው ቀደም ሲል ያደረሰውን ጫና ተከትሎ የንግዱ ማህበረሰብ የደረሰበትን ትንኮሳ በትዕግስት በማለፉ ያመሰገኑት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የህዝቡ ጥያቄ ሀገርን የማፈራረስ ተግባር ተደርጎ ወሬ መነዛቱ የከተማዋን ገጽታ ለማጠልሸት የሚደረግ ዘመቻ በመሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የሀዋሳን ሐይቅ ጨምሮ በሃዋሳ ከተማና በዙሪያዋ በርካታ የልማት አቅም የሚሆኑ ሀብቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሚሊዮን፣ በከተማዋ መጻኢ እድገት የሲዳማን ብሔር ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው በሚል የተነዛው ሀሳብ ከግንዛቤ እጥረትና ቀርቦ ካለመነጋገር የተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

“ ለአንዱ የተሻለ እድል ተሰጥቶ ለሌላው የሚጠብበት ሁኔታ እንዲኖር መስራት ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው” ያሉት አቶ ሚሊዮን ሀዋሳን ለሁሉም የምትመች ከተማ ለማድረግ ተጋግዞ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል ፡፡

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት በከተማዋ ውስጥ የሚስተዋለውን ሕገወጥ አሰራር ለመከላከልና  ሕጋዊና ዘመናዊ የንግድ ሥርአት ለመዘርጋት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በጋራ ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል ፡፡

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ በበኩላቸው የሲዳማን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህዝቡን የሚያሸብሩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የህዝቡን መብት አልፈው ከህግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት ካሉ መንግስት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል ፡፡

የሃዋሳ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ፍስሀ በበኩላቸው በከተማዋ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ቢታቀድም ሊሰበሰብ የቻለው 837 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ለገቢው መቀነስ ተጠቃሽ ምክንያቶች ከሆኑት መካከል አንዱ የንግዱ ማህበረሰብ በነጻነት  ስራውን መስራት ካለመቻል ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ ግብሩን በአግባቡ መክፈል እንዲችል ሰላምና ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርለት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ፍቃዱ፣ መድረኩ ከከተማው አስተዳደር ጋር ለሠላምና ሕጋዊ የንግድ አሰራር መስፈን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግዋል፡፡

ከተሳታፊ የንግዱ ማህበረሰብ መካከል አቶ ፍቅሬ ባፋ ከሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብዥታዎች ሊጠሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት  ፡፡

“ጥያቄውን ተከትሎ የሚፈጠረውን የሌሎች ብሔር ተወላጆች ሥጋትና አለመተማመን ለማስቀረትም የህዝብ ግንኙነት ሥራ መሰራት አለበት” ብለዋል ፡፡

ሌላው ተሳታፊ አቶ ደምቦባ ረጋሳ በበኩላቸው በከተማው ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መወጣት የሚቻለው እርስ በርስ በመደጋገፍ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡

ሕገወጥነትን መከላከል መንግስት ብቻውን የሚሰራው እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ደምቦባ የጋራ ሥራ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አመለክተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የደቡብ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የከተማዋ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም