የጀርመኗ ባየርን ግዛት ከኢትዮጵያጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመኗ ባየርን ግዛት ከኢትዮጵያጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ ሚያዝያ 07/ 2011 የጀርመኗ ባየርን ግዛት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።
በዛሬው እለት የኢትዮ ጀርመን የኢኮኖሚ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ 60 የግዛቲቱ የቢዝነስ ልዑካን እንዲሁም የኢትዮጵያ አቻዎቻቸውና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚሁ ወቅት የባየርን የኢኮኖሚ ጉዳዮች የቀጣናዊ ልማትና ኢነርጂ ሚኒስትር ሚስተር ሮላንድ ዌገን እንዳሉት ከዚህ ቀደም 40 የባየርን የቢዝነስ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር።
የዛሬ ሁለተኛው መድረክ ባየርን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የምታጠናክርበት እንደሆነና የመድረኩ ውይይትም ለዚሁ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ባየርን ከኢትዮጵያ ጋር በሶላር ኢነርጂና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተባብራ እየሰራች ነው ያሉት ሚስተር ርሮላን ሲመንስን የመሰሉ የባየርን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
ግዛቲቱ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላትን ተሳትፎና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አሳውቀዋል።
ወደባየርን ሲመለሱ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት እድል ገለፃ እንደሚያደርጉ ገልፀው ያላቸውን ግንኙነት ዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚመክሩም ተናግረዋል።
ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ቢዝነስ ልዑካን በሙኒክ ከተማ ከባየርን አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን በመግለፅ።
ልዑካኑ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት እንደሚያደርጉና ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም አብራርተዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና በአገሪቱ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተደረገ ስላለው ሪፎርም ገለፃ ተደርገል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያስላሴ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተለዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያና ጀርመን ለብዙ ዓመታት የዘለቀ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረው በየአመቱ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል።
ባለሃብቶች በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚገጥሟቸውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሻሻል እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም እንዲሁ።
በተለይ በማምረቻ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን የሎጅስቲክስ ችግር ለመቅረፍ የግል ባለሃብቱን በዘርፉ ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አገሪቱን ለቢዝነስ አመቺ ለማድረግና ዘርፉን የሚደግፉ አካላት የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ ግዛቲቱ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ ትምህርትና ቴክኖሎጂ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ የመግባቢያ ሰነድም ተፈርሟል።
ኢትዮጵያና ጀርመን ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ግንኙነታቸው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1960 እንደተጀመረ ተገልጿል።