ቀጥታ፡

ሁለተኛው ዙር የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ተጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2011 -የ2011 ዓ.ም ሁለተኛው ዙር ሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከአንድ ወር እረፍት በኋላ ትናንት ተጀምሯል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እና መደወላቡ ዩንቨርስቲ ባደረጉት ጨዋታ መዳወላቡ ዩንቨርስቲ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጋጣሚውን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

ውጤቱንም ተከትሎ መዳወላቡ ዩንቨርስቲ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ ጋር ነጥቡን እኩል 19 ማድረግ የቻለ ሲሆን በግብ ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ወላይታ ድቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፣ ሙገር ሲሚንቶ ከአዲስ አበባ ፖሊስና መከላከያ ከጣና ባህርዳር በሁለተኛው ዙር ሊያደርጓቸው የነበሩ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።

ጨዋታዎቹ የተራዘሙት ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ከአፍሪካ ቮሊቦል የክለቦች ውድድር በመመለሳቸው የእረፍት ጊዜ ለመስጠትና ጣና ባህርዳር ያለበትን የበጀት ችግር እንዲፈታ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የተራዘሙት ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ጊዜ በቀጣይ በሚገለጽ ተስተካካይ መርሃ ግብር መሰረት የሚካሄድ ይሆናል።

በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊጉ ስምንት ክለቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የቮሊቦል ስፖርት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር የውጭ አገራት መምህራን ስፖርቱን እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ። የስፖርቱ መዘውተርም በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል።

ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየውን ቮሊቦል ለማነቃቃት በሁለቱም ጾታ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም