ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር በደሴ ከተማ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር በደሴ ከተማ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2011 ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር ከነገ በስቲያ በደሴ ከተማ ይጀምራል፡፡
በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከ10 ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።
በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የሚደረግባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ውድድሩ ሲካሄድ ሁለት አላማዎችን እንግቦ ነው።
ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭ ማስፋትና በነሐሴ 2011 ዓ.ም በሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመልመል እንደሆነ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ውድድሩ በስፖርቱ ብቁና ውጤታማ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል።
ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንና የመጀመሪያው ውድድር ህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ እና ሁለተኛው ዙር በወላይታ ሶዶ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል።
አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች ውጤት ተደምሮ የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆኑም ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት።
ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።
በጥር ወር 2011 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደው ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ይሰጥ ነበር።
በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር።
በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።
ስፖርቱን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም ተመስርቷል።