ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማጎልበት አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2011በኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማጎልበት አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪና ልጅ ኤቫንካ ትራምፕ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅና አማካሪ ኢቫንካ ትራምፕን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ሥራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

ኢቫንካ ትራምፕ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚደነቁ ናቸው።

የአሜሪካ መንግሥትም በኢትዮጵያ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በተለያዩ መንገዶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት 500 ሚሊዮን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኒሽየቲቭ ይፋ ማድረጋቸውን አማካሪዋ አስታውሰዋል፡፡

ባለፈው የካቲት ወር ይፋ የሆነው ኢኒሼቲቭ የሴቶችን አቅም ማጎልበት፤ የሴቶችን የሥራ ፈጣሪነት እድል ማስፋትና ለሴቶች አጋዥ የሆኑ ህጎችና ደንቦችን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጓል።

በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተቀረጸው ኢኒሼቲቭ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሴቶችን አቅም ለማጎልበት በአዲስና በተለየ የለውጥ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አንስተው በተለይም ሴቶች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በስኬት እንዲያጠናቅቁ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

መንግሥት በሴቶች ዙሪያ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም