አቶ ተስፋዬ ካህሳይና አቶ ጁነዲን ባሻህ ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ

72
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 የትግራይ ክልልን የወከሉት አቶ ተስፋዬ ካህሳይና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን የወከሉት አቶ ጁነዲን ባሻህ በድጋሚ ከሚካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ። ሁለቱ ዕጩዎች "ለአገሪቷ እግር ኳስ ዕድገት ሲባል ራሳችንን ከምርጫው አግልለናል” ብለዋል። በዚህም መሰረት ድጋሚ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የኦሮሚያ ተወካይ አቶ ኢሳያስ ጅራና የአማራ ክልልን የወከሉት አቶ ተካ አስፋው ይወዳደራሉ። ዛሬ በአፋር ሰመራ በተካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ኦሮሚያን የወከሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ 66 ድምጽ በማግኘት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠው ነበር። ይሁንና በምርጫው መመሪያ መሰረት አቶ ኢሳያስ ከተሰጠው 145 ድምጽ አብላጫ ወይም 50 ሲደመር 1 ባለማግኘታቸው የፕሬዝዳንትነት ምርጫው ድጋሚ እንዲካሄድ የምርጫ አስመራጭ ኮሚቴው ወስኗል። ያገኙት ድምጽ ወደ መቶኛ ሲቀየር 46 ከመቶ በመሆኑ ነው ምርጫው እንዲደገም የተደረገው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም