መንግስት የክልሉን ዜጎች የመቻቻል እሴት የሚሸረሽሩ የፖሊስ አባላትን አይታገስም ---የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የክልሉን ዜጎች የመቻቻል እሴት የሚሸረሽሩ የፖሊስ አባላትን አይታገስም ---የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት
አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011 ለዘመናት የቆየውን የዜጎችን የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ለመሸርሸር የሚሞክሩ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የፖሊስ አመራሮችና አባላትን መንግስት እንደማይታገስ የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ከ10 ሚሊዬን ብር በላይ በመመደብ የክልሉን የፖሊስ አመራሮችና አባላት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሁለት ዙር የተሃድሶ ስልጠና እየሰጠ ነው።
ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና የተከታተሉ 514 ተሳታፊዎች ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው በተገኙበት ዛሬ ተመርቀዋል።
በዚህ ወቅት የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ በክልሉ ሙያዊ ሥነ ምግባር በጎደላቸው የፖሊስ አመራርና አባላት ምክንያት ሰላም ጠፍቶ ነበር።
በመሆኑም ትናንት የበደሉትን ህዝብ በእኩልነት በማገልግል እንዲክሱ ክልሉ ለጸጥታ አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት "የተሃድሶ ስልጠና አዘጋጅቷል" ብለዋል።
በፖሊስ ስራ ላይ እጃቸውን የሚያስገቡ አካላት እጃቸውን መሰብሰብ እንዳለባቸው የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ በኋላ የዜጎችን መልካም እሴቶች ለማጉደፍ የሚንቀሳቀሱ እኩይ አካላትን "አንታገስም" ብለዋል።
የተሃድሶ ስልጠናው የለውጡ አንድ አካል መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ የሎጅስቲክስና የስምሪት ስራዎች በለውጡ ቅኝት ማስተካከያ እንደሚደረግባቸው አመልክተዋል።
የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የፖሊስ አመራርና አባላትም ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለያቸው ሁሉንም የክልሉ ዜጎች በእኩልነት እንዲያስተናግዱ ጠይቀዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን ፈታኝ የፀጥታ ስጋት ለማለፍ የፖሊስ አባላትን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቀ ነው አጽንኦት የሰጡት።
በመሆኑን የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት የፖሊስ አመራሮችና አባላትም የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና ሰላም ለማስፈን ከአጎራባች ክልሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ተግባራትን በመታገል ህዝቡና መንግስትን ከወንጀል ስጋት ነፃ ለማድረግ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከለውጡ ጎን እንዲቆሙ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።