በዩኒቨርሲቲዎች የኦዲት ግኝት ጉዳይ ለምን ይበረታል? - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲዎች የኦዲት ግኝት ጉዳይ ለምን ይበረታል?

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ኦዲት ጉድለት አለባቸው በሚል ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ የባለ በጀት መንግስታዊ ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ናቸው።
ከ2002 እስከ 2007 ዓ.ም ለስምንት ዓመታት የተጠራቀመ የኦዲት ግኝታቸውን በ2 ወራት ውስጥ እንዲመልሱ በቅርቡ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
ለመሆኑ በዩኒቨርሲቲዎች የኦዲት ግኝት ጉዳይ ለምን ይበረታል? መፍትሄዎቹስ በሚል ኢዜአ የሚመለከታቸውን ተቋማት አናግሯል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ማቴዎስ ኢንሰርሙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ተቋማት የአንድ መጠነኛ ከተማ ያህል ማህበረሰብ የሚመሩ፣ ውስብስብ የዕውቀት ማዕከላት ናቸው።
የዶክተር ማቴዎስን አስተያይት የሚጋሩት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳነት ዶክተር ኑርለኝ ተፈራ እንደሚሉትም ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የተለየ መሰረታዊ ባህሪያት አላቸው።
ይሁንና ተቋማቱ በተደጋጋሚ የሚነሳባቸው የአዲት ግኝት መንስኤዎች የህግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ በስራ ላይ ያሉት የወጡ የህግ ማዕቀፎች መጣረስና የህግ ማዕቀፎቹ ካላቸው ተልዕኮና ባህሪ አጋር አለመናበብ መሆኑን ይገልጻሉ።
ለአብነትም የትምህርትና ምርመር ተልዕኮ፣ የተማሪዎች ህክምና፣ ምግብና ሌሎች ለ24 ሰዓት የሚፈጸሙ ተግባራት የሚያከናውኑ ተቋማት እንደሆኑ ኃላፊዎቹ ያነሳሉ።
ከህግ ማዕቀፍ መጣረሶች መካከል በ2001 ዓ.ም የወጡት የከፍትኛ ትምህርትና የፋይናንስ አዋጆች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ እንደሆነ ገልጸው፤ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ለአመራርና ቦርድ አባላት ለመወሰን እድል ቢሰጥም ዋና ኦዲተር ተቋማቱን ኦዲት ሲያደርግ ግን ሌሎች ባለበጀት ተቋማት በሚታዩበት የፋይናስ አዋጁን እንጂ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001ን ዕውቅና እንደማይሰጥ ይናገራሉ።
የውጭ መምህራንና አማካሪዎች ክፍያ፣ የህክምና፣ ምግብ፣ እንዲሁም የመማር ማስተማር ግብዓቶች ግዥዎች ተመን አለመኖር ብቻ ሳይሆን አስቸኳይና ድንገተኛ ግዥዎች የአገሪቱን የግዥ ሕጎችን ተከትሎ ለመጸፈም የዩኒቨርሲቲዎች ባህሪ እንደማያስኬድ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች የተለዬ ባህሪ ተለይቶ የመማር ማስተማርና የምርምር ተልዕኮኳቸውን ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ለማዋል የማያሰራ አዋጅን መሻር፣ የቦርድና የአመራሮች ውሳኔ ሰጭነት ነጻነት ከነሙሉ ተጠያቂነት መከበር እንዳለበት ተናግረዋል።
የተሻለ ኦዲት ለመዘርጋት የሰው ሀብት፣ የግዥና ንብረት፣ ተሽከርካሪ፣ የውስጥ ገቢ ተመን የሌላቸውን በቦርድ በማጸደቅ የኦዲት ግኝት ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር ማቴዎስ ገልጸው፤ የገንዘብ አስተዳድሩን ለማዘመን ከገንዘብ ሚኒስቴር የመጣ የተቀናጀ ተፋይናስ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱንና ከ2007 ዓ.ም ኦዲት ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱን አብራርተዋል።
ስህተትና ወንጀል የተለያዩ ናቸው የሚሉት ዶክተር ማቴዎስ ለተቋሙበት ተልዕኮ የሚደረጉ ነገሮች አመራሮች የመሳሳት ነጻነት ይኑራቸው፣ ሃላፊነትና ተልዕኮ ተሰጦ ስለጣን ከተከለከለ ግን አስተዳድሩ መወሰን ያስቸግረዋልና ብለዋል።
ዶክተር ኑርልኝ ተማሪዎችን በፈጠራ ስራ ለማበረታታት ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ የሚሰጠው ሽልማት ሳይቀር ኦዲት እየተደረገ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲውንና ተማሪዎችን ሞራል የሚጎዳ ተግባር መሆኑን ያነሳሉ።
ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የግንባታ ጉዳይ የሚስተዋለው ችግርር ከሌሎች ተቋማት የተለዬ ሳይሆን እንደአገር በዘርፉ ያለው የፕሮጀክት አፈፃፀም ችግሮች በዩኒቨርሲቲዎች ላይ እንደሚከሰት ኃላፊዎች ይናገራሉ።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸሙ ምዝበራዎች ካሉ ሁሉም በጥፋታቸው መጠየቅ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ነገር ግን በጅምላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚሰነዘረው እይታ የተቋማቱን መልካም ስራ የሚያጎድፍ እንደሆነ አብራርተዋል።
የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉ በተደጋጋሚ የሕግ ማዕቀፎ የሌላቸው እንዲወጣላቸው ሲጎተጉቱ እንደነበርና በቅርቡ የማስተካካያ ስራዎች መጀመሩንና የግኝት መጠኑ ሊቀንስ እንደሚችልተናግረዋል።
ነገር ግን ተመን የሌላቸው አሰራሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕግና ስርዓት ኑሯቸው ከሕግ ማዕቀፎቹ ውጭ የሚፈጸሙ ክፍያዎች እንደነበሩ በመግለጽ፣ ከህግና መመሪያ ወጭ አላገባብ ክፈያ የፈጸሙ አመራሮችና ተቋማት ተጠያቂ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
በሳይንስና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አስተዳድርና ሪፎርም ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተፈራም ዩኒቨርሲቲዎች ውስብስብ ስራዎች ያሉባቸው ተቋማት እንደሆኑ ያመናሉ።
ተቋማቱ በአገሪቱ በሚወጡ ሕጎችን ተከተለው እንዲሰሩ ቢጠበቅም፤ ካላቸው ተልዕኮና የተለዬ ባህሪ አንጻር ሁሉንም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በአንድ ስርዓት መምራት ስለማይቻል የራሳቸው የህግ ማዕቀፍ እንዲወጣላቸው እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጣረሱ የህግ ማዕቀፎች ዋና ኦዲተር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ እውቅና አንዲሰጥ የህግ ማሻሻያ ስራዎች እየተደረጉ መሆኑን፣ ተመን ያልነበራቸው 40 ተግባራት ተመን አንዲወጣላቸው መደረጉን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ያቋቋሟቸው የገቢ ማስገኛ ኢንተርፕራይዞች በዋና ኦዲተር ዕውቅና የሌላቸውና ህገ ወጥ በመሆናቸው፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑንና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማጸደቅ እየተሰራ መሆኑን ገለጸዋል።
ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሌሎች ተቋማት ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው ገልጸው፤ነገር ግን ከፕሮጀክቶች ውጭ ያሉ ተግባራት ኦዲት ጉድለት ሲገኝባቸው ሁሉንም በጅምላ ምዝበራ እንዳለባቸው ተደርጎ እንደሚሳል ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለሌሎች ተቋማት ሞዴል እንዲሆኑ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ ከሕግ ማዕቀፍ ችግር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ያላችው እይታ አሉታዊ አንዲሆን ማድረጉን ነው ያነሱት።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት በጀቱ ከፍተኛ ሃብት የሚያንቀሳቅሱ አንደሆኑ ገልጸው፤ በፕሮጀክቶችም ሆነ በሌሎች ስራዎች የምዝበራ ድርጊት የፈጸሙት ተቋማትና ግለሰቦች ተለይተው በሕግ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።
በሥራ ላይ ያለው የከፍተኛ ትምህርት አዋጁ ቁጥር 650/2001 ዩኒቨርስቲዎቹን በአዋጁ ላይ በተቀመጠው የፋይናንስ አስተዳደር መመራት እንዳለባቸው የሚደነግግ ሲሆን፤ በአዋጁ አንቀፅ 66 እና 67 በተቀመጠው መሰረትም በህግ ከተፈቀዱ ሌሎች ምንጮች ገቢዎችን ማሰባሰብ እንደሚችሉ ተቀምጧል።
ይሁንና ዋና ኢዲተር መስሪያ ቤት ዩኒቨርስቲዎች እንደማንኛውም የመንግስት ባለበጀት መስሪያቤት መተዳደር ያለባቸው በፋይናንስ አስተዳድር አዋጅ 648/2001 ብቻ መሆኑን ያስገድዳል።
በከፍተኛ ትምህርት አዋጁና በፋይናንስ አዋጁ ላይ የተፈጠረው ክፍተትም ታድያ ተቋማቱን ለኦዲት ችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
ይህም በሕግ ትርጉም አተያይ ዩኒቨርሲቲዎች ከፋይናንስ አስተዳድር አዋጅ በኋላ በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቢዳኙበትና ቢመሩሩበት ተቀባይነት እንደሚኖረው የሚገለጹ አሉ።
ከፋይናንስ አስተዳድር አዋጁ ጋር የተቃረነው የከፍተኛ ትምህረት አዋጅም ተገቢው ማሻሻያ ተደርጎለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ተገልጿል።