ቀጥታ፡

በአቢጃን የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 82 አትሌቶችን ታሳትፋለች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011 በኮቲዲቫር አቢጃን ከተማ በ14ኛው የአፍሪካ ታዳጊዎችና ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 82 አትሌቶችን ታሳትፋለች።

በዚህ ውድድር የሚካፈሉ አትሌቶችና 14 አሰልጣኞችን ጨምሮ በድምሩ 111 የሉዑካን ቡድን አባላት ትናንት ምሽት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጊዜዊ ፕሬዚዳንት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ ''በስፖርት ማሸነፍ እንዳለ ሁሉ መሸነፍም ያለ ቢሆንም የቡድኑ አባለት የማሸነፍ ወኔ ይዞ መሄድ ይገባዋል'' ብላለች።

አትሌቶች በልምምድ ጊዜ የነበረቸውን ጥሩ ስነ ምግባር በውድድሩ ቦታም ማሳየት እንዳለባቸው መክራለች።

የኢትዮጵ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ስፖርቱ ለሰላምና ለሀገር እድገትም ያለውን ጠቀሜታ ትልቅ መሆኑን በማውሳት በዚህ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች ይህን ተረድተው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በስነ -ልቦና መዘጋጀት ይገባቸዋል ብለዋል።

በዚህ ሽኝት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤትና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩት አቶ በላይነህ ክንዴ ውጤታማ ለሚሆኑ አትሌቶች በግላቸው የገንዘብ ሽልማት እንደሚያበርከቱ ቃል ገብተዋል።

ለሀገራቸው ወርቅ ለሚያመጡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር ፣ የብር ሜዳሊያ ለሚያመጡ 3 ሺህ ብር፣ የንሐስ ሜሊያ ለሚያመጡ 2 ሺህ ብርና ለአሰልጣኞችም በተመሳሳይ ሽልማት አበረክታለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር በአጭር ፣ መካከለኛ፣ ረጅም ርቀትና በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባራት በሆኑት በውርወራና ዝላይ  የምትካፈል ይሆናል።

በዚህ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች እድሜቸው ከ18 እና 20 ዓመት በታች ያሉ አትሌቶች ሲሆን ባለፉት 45 ቀናት በሆቴል ከትመው ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

14ኛው የአፍሪካ ታዳጊዎችና ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊታች ማክሰኞ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአቢጃን ይካሄዳል።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውን ውድድር ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም