የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባ ተመለከተ
ዲላ ሚያዚያ 5/2011 የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጠበቅ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
የጌዴኦ ዞን ጸጥታ ምክር ቤት ከፍትህና ጸጥታ ተቋማት ከተወጣጡ ተወካዮች ጋር ስለ ዞኑ የጸጥታ ሁኔታ በዲላ ከተማ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ወቅት የምክር ቤቱ አባል አቶ ተካልኝ ታደሰ እንዳሉት በአጎራባች አካባቢዎች የህግ የበላይነትን በማስከበሩ ረገድ ባሉት ውስንነቶች ለዜጎች ደህንነት ሰጋት ሆኗል፡፡
በአጎራባች አካባቢዎች የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን የጸጥታ ስጋት መቀነስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በበኩላቸው የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች የህብረተሰቡን የሰላም እሴት በመገንባትና እርቅ በማውረድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ካልቻለ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
"የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የህግ የበላይነትን በማረጋገጡ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመናበብና በቅንጅት መፍታት ይገባል" ያሉት ደግሞ የዞኑ ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ስዩም ናቸው፡፡
የ32ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ይልማ አብርሃ በአጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ወራት በተወሰደው ስርዓት የማስከበር እርምጃ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ቄያቸው መመለስ ካልተቻለ የክረምቱ ዝናብ መምጣት ከሰብዓዊ አቅርቦት እጥረት ጋር ተዳምሮ ለከፋ ጉዳት ሊዳርጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ስራዊት በየደረጃው ካለ የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱና ህዝባዊ ውይይት በመደረጉ ተፈናቃዮችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
"በአካባቢዎቹ የሚከሰቱ ትንኮሳዎችና ዛቻዎች በጸጥታው ኃይል ብቻ ማስቆም አይቻልም " ያሉት ሌተናል ኮሎኔል ይልማ ህዝቡ እንዲያግዛቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፀጥታና የፍትህ መዋቅሩ የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በአመለካከትም ሆነ በተግባር ዝግጁ መሆን እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡
ከተመሰረተ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው የዞኑ የጸጥታ ምክር ቤት የፍትህ ተቋማትን፣መከላከያ ሰራዊትና ሌሎችም አካላት አባል እንደሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡