ቀጥታ፡

አርባ ምንጭ ከነማ ፕሪሜየር ሊጉን ለመቀላቀል በሚያስችለው አቋም ላይ መሆኑን ገለፀ

አርባምንጭ ሚያዝያ 5/2011 አርባ ምንጭ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ዳግም የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግን ለመቀላቀል በሚያስችለው አቋም ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

ክለቡ ዘንድሮ እየተሳተፈ  ባለው የከፍተኛ ሊግ ባደረገቸው 13 ጨዋታዎች25 ነጥብ በማስመዝገብ  ከመሪው ከሃዲያ ከነማ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የክለቡሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ስንታየሁ ደግፈ ለኢዜአ እንደገለፁት ክለቡ ከፕሪሜየር ሊግ መውረዱ በአመራሩ፣ ተጫዎቾችና ደጋፊዎች ዘንድ ቁጭት ፈጥሯል ።

"የቡድኑ አባላት እርስ በርስ ግንኙነት ጤናማ አለመሆን፣ በየጊዜው አሠልጣኝ መቀያየርና የውድድሮች መቆራረጥ ለክለቡ ከፕሪሜየር ሊጉ መውረድ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል ።

ክለቡ የነበሩበትን ችግሮች ለማስተካከል የተሻለ ልምድ ያለው አሠልጣኝ የመቅጠር፣ ክለቡን በወጣት ተጫዋቾች የማደራጀት፣የገንዘብና አቅምን የማጠናከር ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑን ጠቅሰዋል ።

አሁን ላይ የተጫዋቾች ብቃትና ክለቡ ያለበት ደረጃ መልካም  መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ "ያጣነውን ክብር ዳግም ለመጨበጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅትና ውድድር እያደረግን ነው" ብለዋል ።

የአዞዎቹ አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው  ከተስፋ ቡድን የተመረጡ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በማቀላቀል ተጫዋቾችን በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል ።

"የክለቡ ተጫዋቾቹ ስነ-ምግባርና ሜዳ ላይ ጎል የማስቆጠር ብቃት ጠንካራ ሆኗል" ያሉት አሠልጣኝ መሳይ ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች በ12ቱ ጎል ማስቆጠሩን ጠቅሰዋል ።

"ከዚህ ቀጥሎ በሚኖሩ ዘጠኝ ጨዋታዎች ዙሩ እየከረረ የሚመጣ በመሆኑ በጥንቃቄ በመጫወት ውጤት እናስመዘግባለን " ብለዋል ።

"የተጫዋቾችና አሠልጣኝ ግንኙነት ቤተሰባዊ በመሆኑ በክለቡ ጠንካራ የቡድን መንፈስ ተፈጥሯል" ያለው ደግሞ  የቡድኑ አንበል ወርቅይታደስ አበበ ነው ፡፡

 በመጪው ዓመት ፕሪሜየር ሊጉን ለመቀላቀል አቅም የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጿል።

በተለይ የአርባ ምንጭ ከተማና የጋሞ ዞን አስተዳደር አካላት በስነ ልቦናና በገንዘብ እያደረጉ ያለው ድጋፍ  ለክለቡ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑም ጠቅሷል፡፡ 

አዞዎቹ ዛሬ ጅማ ላይ ከጅማ አባቡና ጋር የከፍተኛ ሊግ ጨዋታቸውን ያካሄዳል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም