ዛሬ በተጀመረው የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ውድድር ሁለት ጨዋታዎች ተካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
ዛሬ በተጀመረው የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ውድድር ሁለት ጨዋታዎች ተካሄዱ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2011 የኢትዮጵያ ጠርጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሸን ዓመታዊ ውድድር የሆነው የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ውድድር ዛሬ ሲጀመር ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል።
ውድድሩ ለአገሪቱ ጠረጴዛ ቴኒስ እድገት ሲሰሩ በነበሩት ባለፈው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት ኢንስትራክተር ከበደ ሙሉጌታ ስም ተሰይሟል።
ለሶስት ወራት የሚካሄደው ይህ ውድድር በአዲስ አበባ በአራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ጨምሮ በሶስት የተለያዩ የስፖርት ትምህርትና ስልጠና መስጫ ማዕከላት ውድድሩ ይካሄዳል።
በዚህ ጨዋታ ስምንት ቡድኖችና ሶስት ክለቦች በአዋቂና በወጣት ቡድኖች በሁለቱም ጾታዎች የሚካፈሉ ይሆናል።
ዛሬ በመክፈቻው በአዋቂ ወንዶች ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከየኔነህ አዲስ የተጫወቱ ሲሆን በውጤቱም ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ሁለተኛው ጨዋታ በወጣት ሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባደረጉት ጨዋታ ንግድ ባንክ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ውድድሩ በስማቸው የተሰየመላቸው ኢንስራክተር ከበደ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ከ10 ዓመት በላይ በተጫዋችነት ከዚያም በኋላ በአሰልጣኝነት እስከ 2004 ዓ.ም አገልግለዋል።
በአሰልጣኝነትና በብሄራዊ ቡድን ተጫዋችነት አገራቸውን ወክለው መሳተፍ የቻሉ ሲሆን ታዳጊዎችን አሰልጥነው ተተኪዎችን በማፍራት ይታወቃሉ።
በ1966 ዓ.ም በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ በተደረገው የግል የበላይነት የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍለው ሜዳሊያ ማምጣት ችለዋል።