ቀጥታ፡

የኮንስትራሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚያካሄዳቸውን ግንባታዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲያጠናቅቅ ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2011 በኮንስትራሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እየተካሄዱ ያሉ የህንፃ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠናቀቅ እንደሚገባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኮንስትራሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የስራ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ ለመፈተሽ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

ቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ካደረገባቸው የኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶች መካከል የመለስ ዜናዊ አካዳሚ፣ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እና የተለያዩ የህንጻ አካላት ማምረቻ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ወይዘሮ ናፈኩሽ ደሴ እንድገለጹት፤ በአገር ውስጥ  የኮንስትራክሽን ምርቶች በማምረትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያካሂደውን ጥረት አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ  ፕሮጀክቶችን በተቀመጣላቸው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ በኩል ጉድለቶች አሉ፤ ይህ ደግሞ አገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ እና ኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ የህንፃዎቹ ግንባታ በአፋጣኝ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሊበቃ ይገባል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክት እንቅስቃሴ፣ የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም  አመላክተዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ አብጠው በበኩላቸው፤ በኮርፖሬሽኑ አማካኝነት የመንገድ ግንባታና ጥገና፣ የከፍተኛ ድልድይ  የአየር ማሪፊያና ሌሎች የሲቪል ግንባታ ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን አብራርተዋል።

አሁን ላይ እየተገነቡ ላሉት ፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየት አንዱ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከውጪ ለግብዓትነት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለማምጣት እክል መፍጠሩን አንስተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራር ተከትሎ በራስ አቅም መስራት የሚቻልበት ሁኔታዎች በአገር ውስጥ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ይህም የተቋሙ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱ፣ የመንግስትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም