ቀጥታ፡

በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ገቢ ለማሰባሰብ ቃል ገቡ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2011 በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ገቢ ለማሰባሰብ ቃል ገቡ።

በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኬንያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው ኢትዮጵያዊያኑ ቃል የገቡት።

በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም  በኬንያ የሚካሄደውን የትረስት ፈንድ ዝግጅት በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ፕሮግራሙን የሚያስተባብር ኮሚቴ በማቋቋም ዝግጅት እያደረጉ ነው ተብሏል።

በሀገራቸው ለተጀመረው ለውጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል። 

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በውጪ የሚኖሩ ዜጎች የሀገራቸው እንደራሴ በመሆናቸው በገጽታ ግንባታ፣ ልማት እና ሌሎችም መስኮች አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በኬንያ የሚገኘው ሚሲዮን እንደተለመደው ዜጎችን ለማገዝ እንደተዘጋጀም ገልጸዋል።

አምባሳደር መለስ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ ቢያንስ አንድ ዶላር በመለገስ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የ2011 ዓ.ም አገራዊ በጀትን ባጸደቁበት ወቅት ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ላይ እንዲሳተፍ በቀን የ1 ዶላር መዋጮ መጠየቃቸው ይታወሳል።

በትረስት ፈንዱ አማካኝነት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ገንዘብ መሰብሰብ የጀመረ ሲሆን እስካሁን ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰብስቧል።

በሌላ በኩል በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ባሳለፍነው ሳምንት ከኤርትራ አምባሳደር በየነ ርዕሶም፣ ከሱዳን አምባሳደር ጋሪባሊ ከድር አሊ፣ ከደቡብ ሱዳን አምባሳደር ቾል አጆንጎ እንዲሁም ከጅቡቲ አምባሳደር ያሲን ኤልሚ ቡህ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ያተኮረው በኢትዮጵያና በአገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት እና የቀጠናውን ትስስር ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገድ ላይ ነው።

በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋም ሆነ ግንኙነቷ ጎረቤት-ተኮር እንደሆነ ተናግረዋል።

ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ኢትዮጵያ አጽንኦት ሰጥታ ትሰራለች ሲሉም አክለዋል።

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አዎንታዊ ለውጥ በቅርበት እንደሚከታተሉ፣ አገሮቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉና ለዚህም በናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ የኤምባሲው መግለጫ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም