ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ 20ኛ ሳምንት መቐሌ 70 እንደርታና ባህርዳር ከተማ ይጫወታሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 5/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሃ ግብር መቐሌ 70 እንደርታ ከባህርዳር ከተማ ጋር ነገ ይጫወታሉ።

ፕሪሚየሪ ሊጉ ዛሬ በመቀሌ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመከላከያ ይጫወታሉ፡፡

ቀሪ ሰባት የሊጉ ጨዋታዎች ነገ  ይካሄዳሉ።

ከ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በአዲስ አበባ አንድ ጨዋታ ሲደረግ ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በክልል ሜዳዎች የሚደረጉ ናቸው።

ነገ  በሊጉ በ29 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ የሊጉ መሪ የሆነውን መቐሌ 70 እንደርታን በባህርዳር ስታዲየም ይገጥማል።

ይህ ጨዋታ መቀሌ ከተከታዮቹ ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚደረግ በመሆኑ በሳምንቱ ካሉ ጨዋታዎች መካከል እጅግ የሚጠበቅ ሆኗል።

እንዲሁም ሁለቱ ክለቦች ባላቸው የደጋፊ ብዛት በሜዳ ላይ የሚፈጥሩት የድጋፍ ድባብ ጨዋታውን አጓጊ ያደርገዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሊጉ በ30 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሲዳማ ቡና ጋር የሚደረጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድ ሲሆን ጅማ አባጅፋር ከስሁል ሽረ ጋር  ይጫወታሉ።

ደደቢት ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የሚጫወት ሲሆን ፋሲል ከነማ ከደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚረሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በክልል የሚደረጉ ጨዋታዎች ከቀኑ በ9 ሰዓት የሚደረጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ደግሞ ከቀኑ በ10 ሰዓት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም