ቀጥታ፡

ፓርቲዎቹ የተስማሙበትን የጋራ ቃልኪዳን ለማስፈጸምና የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ሰነድ አጸደቁ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2011 ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የቃልኪዳን ሰነዳቸውን ለማስፈጸምና የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ሰነድ ተወያይተው አጸደቁ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የውስጥ የስራ አፈጻጸም ደንብና የቃልኪዳን ሰነድ ለማስፈጸም የወጣ የስነ ስርአት ደንብ ናቸው ዛሬ በተካሄደው ውይይት የፀደቁት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የውሰጥ የስራ አፈጻጸም ደንብ አምስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም የቃል ኪዳን ሰነድ በፈረሙ ፓርቲዎች ሁሉ ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይደነግጋል።

ደንቡ የምክር ቤቱ የስራ አመራርና አሰራር፣ የኮሚቴ አይነት፣ የአባላት የስራ ዘመንና ግዴታ፣ በጀትና ሌሎች ጉዳዮችን አካቷል።

የቃልኪዳን ሰነዱን ለማስፈጸም የወጣው የስነ-ስርአት ደንብም በተመሳሳይ አምስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን አቤቱታ በቀረበበት ማንኛውም ፓርቲ ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ያትታል።

ይህንን የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድ የጣሰ ሲኖር ይህን የተመለከተ አቤቱታና ማስረጃ አቀራረብ፣ የቀረበው ማስረጃና አቤቱታ እንዴት ይታያል፣ ውሳኔው እንዴት ይሰጣል፣ የሚሰጡ ቅጣቶችና አማራጮች ምንድን ናቸው በሚለው ላይም ውይይት ተካሂዷል።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ተወካዮች በደንቦቹ ላይ መጨመርና መቀነስ አለባቸው ያሏቸውን ሃሳቦች አንስተው ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የፓርቲዎች የቃልኪዳን ሰነድ መፈጸም ያለበት በራሳቸው በፓርቲዎቹ ነው ብለዋል።

ለዚህም እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና ጥፋተኛን በራሳቸው የማረም ሂደትን ለማጠናከር የጋራ ምክር ቤት በማስፈለጉ ይህን ማቋቋም ይቻል ዘንድ ሰነዶቹ ተዘጋጅተዋል።

አፈጻጻሙ በፓርቲዎች የሚከናወን ሲሆን ሰላምን ለማስጠበቅ፣ በዜጎች መካካል ያለውን ውይይት ለማዳበርና ለምርጫም ዝግጅት ያግዛል ሲሉ አክለዋል።

ውይይቱ ነገም የሚቀጥል ሲሆን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰምሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ጸሃፊ በመምረጥ በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ላይ ውይይት ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም