ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ለተቀበለቻቸው የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦች ተፈፃሚነት እየተሰራ ነው

አዳማ ሚዝያ 4/2011 ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ለተቀበለቻቸው የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦች ተፈፃሚነት እየተሰራ መሆኑን  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሁሉ አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ ለኢትዮጵያ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች አፈፃጸም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተወያይቷል።

በዚህ ወቅት በኮሚሽኑ የምክርና ክትትል ባለሙያ አቶ ግርማዬ ነጋሽ እንዳስታወቁት በዓለም ያለውን የሰብአዊ መብት ጥበቃ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስን ዓላማ ባደረገው በሁሉን አቀፍ ተከታታይ የግምገማ ሥርዓት ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሪፖርት አቅርባለች።

"ሪፖርቱ ሀገሪቱ በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ባለፉት አራት ዓመታት ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በመለየት ለመፍታትና ያላትን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ያመላከተ ነው" ብለዋል።

ሪፖርቱን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢኮኖሚ፣ማህበራዊና የባህል መብቶች ዙሪያ ምክረ ሀሳቦች መስጠቱን ጠቁመዋል።

በተለይ ሰብአዊ መብቶን ለመጠበቅ በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት ባለፉት አራት ዓመታት በህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኩል ከመጡ አቤቱታዎች ውስጥ 3 ሺህ 596 እልባት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ባለሙያው እንዳሉት በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት  ላይ በተሰጠው ምክረ ሃሳብም  ማሻሻያዎች ተደርጓል፤ ከነዚህም ውስጥ አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መጽደቁን፣  የትምህርትና ስልጠና የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

የባህልና የኃይማኖት ነፃነት መብት ምክረ ሀሳብ መሰረትም አለመቻቻል ለማስወገድ ባለፈው ዓመት ከ40 ሚሊዮን ከሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

የተደረገው ውይይትም በሰላም እሴት ግንባታ፣ስለአክራሪነትና ጽንፈኝነት አደጋዎችና የመከላከያ ስልቶችና በሌሎችም ዙሪያ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ በበኩላቸው ሁሉ አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ልዩ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህ የግምገማ ሂደት ሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶችን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሻሻልና በማሟላት ረገድ የገጠማትን ተግዳሮት ለመቅረፍ የወሰደችውን የእርምት እርምጃ ለመግለጽ ሰፊ እድል እየፈጠረ ይገኛል" ብለዋል።

የተለያዩ ሀገራትን መልካም ተሞክሮዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ለመለዋወጥ በዓይነቱ ለየት ያለ መድረክ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ በተደረገው ግምገማ መሰረት ቀሪ ስራዎች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከኮሚሽኑ ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ  ናቸው።

የፌዴራል ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ከመድረኩ መነሻ የሚሆን ሀሳብ እንዳገኙ  እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም