ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓመቱ የመጨረሻ ውድድሩን ዛሬ አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓመቱ የመጨረሻ ውድድሩን ዛሬ አካሄደ
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ ባደረገው የዱላ ቅብብል ውድድር የ2010 ዓ.ም የጎዳና ላይ ሩጫ መርሃ-ግብሩን አጠናቀቀ። የዛሬው ውድድር "የትራፊክ አደጋን በጋራ እንከላከል የመንገድ ደህንነት ለሁላችን" በሚል መሪ ሀሳብ ለ15ኛ ጊዜ የተካሄደ ነው። በዱላ ቅብብሉ ላይ ከ75 የአትሌቲክስ ክለቦች፣ ከ50 ድርጅቶችና 25 ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከተመሰረቱ ቡድኖች ከ1 ሺህ 200 በላይ ተሳታፊዎች ተወዳድረዋል። የዱላ ቅብብሉ መነሻውን ብስራተ ገብርኤል አደባባይ አድርጎ በመካኒሳ አቦ ማዞሪያ በማድረግ ብስራተ ገብርኤል አደባባይ ተጠናቋል። በአትሌቲክስ ቡድኖቹ መካከል የተካሄደው የዱላ ቅብብል 12 ኪሎ ሜትር ሲሆን እያንዳንዱ የአትሌቲክስ ቡድን ተወዳዳሪ በየሶስት ኪሎ ሜትሩ ዱላ ተቀባብሏል። ከድርጅቶችና ከህብረተሰቡ የተወጣጡ ቡድኖች የሚያደርጉት ውድድር የስድስት ኪሎ ሜትር ሲሆን በየአንድ ኪሎ ሜትሩ ዱላውን ተቀባብለዋል። ከብስራተ ገብርኤል አደባባይ እስከ መካኒሳ አቦ ማዞሪያ ያለው ርቀት 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ሲሆን አትሌቶቹ በመነሻውና በመድረሻው አራት ጊዜ ደርሶ መልስ ሲያደርጉ የድርጅትና የህብረተሰቡ ተሳታፊዎች ሁለት ጊዜ ደርሶ መልስ አድርገዋል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለጹት የውድድሩ ዋንኛ ዓላማ በመንገድ ደህንነትና ትራፊክ አደጋን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው። በዱላ ቅብብል ውድድሩ ላይ አንድ አሽከርካሪ ጠጥቶ መንዳት እንደሌለበት፣ ዜጎች በእግረኛ መንገድ ላይ መጓዝ እንዳላባቸውና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ራሱን ከአደጋ በመጠበቅ በደህንነት መኖር አለበት የሚሉ መልዕክቶች ሲተላለፉ ነበር። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የመንገድ ደህንነት እንዲጠበቅና የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ውድድሩ ጠንካራ የቡድን መንፈስ እንዲኖርና በሰዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ ቀረቤታ እንዲጎለብት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በአጠቃላይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 12 ውድድሮችን እንዳካሄደና ቁጥሩ ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንደሆነም አመልክተዋል። በቀጣይ ዓመትም በየዓመቱ ከሚካሄዱ መደበኛ ውድድሮች በተጨማሪ በባህርዳርና በመቀሌ ከተሞች አዲስ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን ለመጀመር ማቀዱንም ነው አቶ ኤርሚያስ ያስረዱት። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው የዱላ ቅብብል ውድድሩ በስፖርቱ ከመዝናናትና ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ የትራፊክና የመንገድ ደህንነት መረጃዎች ለህብረተሰቡ በተሻለ መልኩ እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል። በመዲናዋ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በቂ አለመሆናቸውንና እንዲህ አይነት ውድድሮች መልዕክቶቹ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። ኮሚሽኑም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለሀብረተሰቡ የትራፊክና የመንገድ ደህንነትን አስመልክቶ መልዕክቶች እያስተላለፈ መሆኑንና በቀጣይም ይሄንኑ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በአትሌቶች የዱላ ቅብብል በቡድን ወንዶች መከላከያ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። በአትሌቶች የዱላ ቅብብል በቡድን ሴቶች ቡድን ኤ እና ቢ በሚል ሁለት ቡድኖችን ያሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ያወዳደራቸው ኤ እና ቢ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ መከላከያ ሶስተኛ ወጥቷል። በአትሌቶች የዱላ ቅብብል በቡድን ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ክለቦች እንደየቅደም ተከተላቸው የ10፣ የስድስት እና የአራት ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በድርጅቶችና ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች የዱላ ቅብብል ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ቡድኖች የዋንጫ ሽልማት እንዲሁም ውድድሩን ላጠናቀቁ ሁሉም ቡድኖች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የስራ ኃላፊዎች ሽልማቱን ለአሸናፊዎች አበርክተዋል። በ1994 ዓ.ም የተመሰረተው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እስካሁን 137 ውድድሮች አካሂዷል።