የመገናኛ ብዙሀን ፖሊስና የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂክ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሀን ፖሊስና የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂክ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ
አዳማ ሚያዝያ 4/2011 የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ነባራዊ ሁኔታና ገፅታን ለመቀየር የሚያስችል ረቂቅ ፖሊስና ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
ለዚህ የመገናኛ ብዙሀን ፖሊስና የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂክ ረቂቅ ሰነድ ማጎልበቻ ግብዓት ለማሰባሰብ ለግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስትንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በመድረኩ እንደገለፁት በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን ኢንዱስትሪው የሚመራበት ፖሊስና የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂክ እቅድ አልነበረም።
የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊስና ስትራቴጂ ሰነድ የመገናኛ ብዙሀን ዘርፉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት የዳሰሰ ከመሆኑም ባለፈ አጠቃላይ ገፅታውን የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል።
"ረቂቅ ሰነዱን የማያዳበርና የሚያሻሻሉ ሃሳቦች በግብዓትነት ለማሰባሰብና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ታስቦ የውይይት መድረኩ ተዘጋጅቷል" ብለዋል ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ -ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊና የረቂቅ ሰነድ የዝግጅት ኮሚቴ ቡድን አባል ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በውይይት መድረኩ የረቂቅ ሰነዱን ዝርዝር ሀሳብ አቅርበዋል ።
"ሰነዱ የተዘጋጀው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ኢንዱስትሪ የሚመራበት ህግና መመሪያ እንዲኖረው ለማስቻል ነው" ብለዋል ።
የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን ኢንዱስትሪ ያሉበት ችግሮች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ጥናት በማድረግና የውጭ ሀገር ተሞክሮ በማካተት ሰነዱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
"በጥናቱ በዘርፉ ልማት ያሉ ማነቆዎችና አማራጮች የተዳሰሰበት ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ሰነዱ የመገናኛ ብዙሀን ነባራዊ ሁኔታና ገጽታ ከመሰረቱ መቀየር እንደሚያስችል አስረድተዋል።
የዜጎች መረጃ የማግኘት፣ የባለስልጣኑ የፍቃድ አሰጣጥና አሰራር፣ የመገናኛ ብዙሀን ከተፅእኖ ነፃ ሆነውና ሀገራዊ ህጉን ተከትሎ መመራት የሚችሉበት ሁኔታዎች በሰነዱ በዝርዝር ተካቷል።
የጋዜጠኝነት ትምህርትና ስልጠና፣ ለሙያውና ለጋዜጠኞች የሚደረግ ከለላ የተመለከቱ ጉዳዮችም በሰነዱ ተመላክቷል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ የፌደራልና የክልል መገናኛ ብዙሀን ተቋማትና በዘርፉ የተሰማራው የግሉ ሴክተር ከመናቆር የሚወጡበት፣ ሀገራዊ የዴሞክራሲ ምህዳር ተጠናክሮ የሚቀጥልበትና የመገናኛ ብዙሀን የይዘት ሥራዎች ይበልጥ የሚጎለብቱበት ሁኔታዎች በሰነዱ ተዳሰዋል ።
ረቂቅ ሰነዱ ከዳበረ በኋላ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለፖሊሲ አውጭ አካል እንደሚቀርብ ታውቋል ።