የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች ያደረገውን ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች ያደረገውን ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አስረከበ
ሀዋሳ ሚያዝያ 4/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደቡብ ክልል ተፈናቃዮች ያደረገውን ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለክልሉ ርዕስ መስተዳድር አስረከበ፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ዲና በርክክቡ ወቅት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው የዜጎች መፈናቀልና በደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃና በማህበራዊ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅርበት እያጠና የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት 100 ሚሊዮን ብር መለገሱን አስታውሰዋል፡፡
ከፌዴራል አደጋ ስጋት ኮሚሽን በተገኘ የተፈናቃይ ቁጥር መነሻም 18 ሚሊዮን 304 ሺህ ብር በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል መወሰኑን አስረድተዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው የተከሰተው ሰው ሰራሽ አደጋ በሽግግር ውስጥ እንደሚያጋጥም ጠቁመው ችግሩን ለማለፍ በሚደረገው ጥረት የገንዘብ ተቋማት እገዛ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
" ባንኩ ለተፈናቃይ ወገኖች ያደረገው ድጋፍ የህዝብ ባንክ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው" ብለዋል።
የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ በክልሉ በከተማና ገጠር አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን ከመደገፍ ባለፈ ለሕብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ማደግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትም አቶ ሚሊዮን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡