ቀጥታ፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚለኒየም ህክምና ኮሌጅ ሁለት ከያኒያንን አምባሳደሩ አድርጎ ሰየመ

አዲስ አበባ  ሚያዝያ  4/8/2011 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚለኒየም ህክምና ኮሌጅ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሳደግ ያግዙት ዘንድ ሁለት ሴት ታዋቂ ከያኒያንን የሆስፒታሉ አምባሳደሮች አድርጎ ሰየመ።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አምባሳደር የተደረጉት ድምፃዊት ፀደኒያ ገብረማርቆስን እና ደራሲና ተዋናይ አዜብ ወርቁ ናቸው።

አምባሳደሮቹ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ኀብረተሰቡ ስለጤና አጠባበቅ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ። 

ከዚህም ባሻገር አዜብ ወርቁ የእናቶችና ህፃናት ህክምና አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በማተኮር የምትሰራ ሲሆን ድምፃዊት ፀደኒያ ደግሞ የሆስፒታሉ የፅዳት ሁኔታ በሚሻሻልበት መንገድ ላይ ታገለግላለች ተብሏል።

ሆስፒታሉ ዛሬ ከከያኒያኑ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፤ በቀጣይ ተግባራቸው ላይም ከሆስፒታሉ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት የኮሌጁ የሜዲካል አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ሊዲያ ተፈራ ሆስፒታሉ በዘመናዊ መሳሪያ በመደራጀትና በስፔሻሊስት ባለሙያዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የሚስተዋሉበት ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በተለይም በጽዳት፣ በእናቶችና ህፃናት ህክምና ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት አምባሳደሮቹ ሚናቸው ከፍ ያለ እንደሚሆን ገልፀዋል።  

የሆስፒታሉ ሰራተኞች በህክምና ስራቸው ላይ በመጠመዳቸው ሳቢያ ያላስተዋሏቸው ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲፈቱ ለማድረግ የአምባሳደሮቹ ሚና የላቀ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በሆስፒታሉ የሚታቀዱ ስራዎች ክንውን ምን ላይ እንደደረሰ ይቆጣጠራሉ፤ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም ያመላክታሉ ሲሉም ገልፀዋል።

አምባሳደሮቹ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ኀብረተሰቡ ስለጤና አጠባበቅ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግም ይሰራሉ ነው ያሉት ዶክተር ሊዲያ።

ከአምባሳደሮቹ ጋር ስምምነት መፈራረም ያስፈለገው ሆስፒታሉን ወክለው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እውቅና እንዳላቸው ለማሳወቅ መሆኑንም ተገልጿል።

ከያኒያኑ በበኩላቸው በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ስምና ሙያቸውን ተጠቅመው ኀብረተሰቡን ለማስተማርና ግልጋሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሆስፒታሉ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በመጠቀም አገልግሎቱን ለማሻሻል ማሳቡ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን አክለዋል። 

ድምፃዊት ፀደኒያ እንዳለችው ከዚህ በፊት በሌሎች ተቋማት አምባሳደር በመሆን ከሪፖርት ማሟያነትና በዓል ማድመቂያነት ያለፈ ተግባር እንዳልነበራት ገልፃ አሁን ግን ሆስፒታሉ ቋሚ የመገናኛ ጊዜና የትኩረት ዘርፍ መስጠቱ ስራው በትክክል እንደሚሰራ አመላካች ነው ብላለች።

ደራሲና ተዋናይ አዜብ ወርቁ በበኩሏ ሆስፒታሉ በተጠቃሚውና በተቋሙ መካከል ያሉ ክፍተቶችን እንድናሳይ ሶስተኛ አይንና እጅ ሆነን እንድናግዝ ጠርቶናል ነው ያለችው።

ሆስፒታሉ በቀጣይ በአምባሳደሮቹ አስተባባሪነት የጽዳትና የደም ልገሳ ዘመቻ እንደሚያካሂድም ታውቋል።

አምባሳደሮቹ ለቀጣይ ሁለት አመት አገልግሎት እንደሚሰጡም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም