ቀጥታ፡

ምግብን ከባእድ ነገር ጋር ይደባልቃሉ ተብለው በተጠረጠሩ 63 ተቋማት ላይ ምርመራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዝያ  4/2011 ምግብን ከባእድ ነገር ጋር በመደባለቅ ለገበያ ያቀርባሉ ተብለው በተጠረጠሩ 63 የምግብ አቅራቢ ተቋማት ላይ ምርመራ መጀመሩን የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ተቋማቱ ጤፍን ከጄሶና ከተፈጨ ሰጋቶራ ጋር በመደባለቅ የተጋገረ እንጀራ፤ በርበሬ፣ ማርና ቂቤንም ከተለያዩና ምንነታቸው ከማይታወቅ ባእድ ነገር ጋር በመቀላቀል ለገበያ በማቅረብ የተጠረጠሩ ናቸው።

ምግብን ከባእድ ነገር ጋር እያቀላቀሉ ለተጠቃሚ የማቅረብ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ አካላት በህግ አስከባሪ አካላት መያዛቸውን በመገናኛ ብዙሃን መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ለሰው ጤናና ህይወት አደገኛ የሆኑ ባእድ ነገሮችን ከምግብ ጋር በመቀላቀል፤ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ ለምግብ መዋል የሌለባቸውን ንጥረ ነገሮች አንድን ዓይነት የምግብ መልክና ቅርፅ በመስጠት ለህዝቡ እየቀረቡለት መሆኑም እየተነገረ ነው።  

በዚህም የተነሳ በርካታ ተጠቃሚዎች የሚቀርብላቸው ምግብ ነክ ምርት ደህንነቱ አስተማማኝ ሰለመሆኑ እርግጠኞች መሆን እንዳልቻሉና ሁሌም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ሲገልፁ ይደመጣል። 

እናም የኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ምግብን ከባእድ ነገር ጋር እየቀላቀሉ ለተጠቃሚ የማቅረብ ተግባር ለመከላከል ያግዛል ያለውን ኦፕሬሽን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ላለፉት ዘጠኝ ወራት ማካሄዱን ዛሬ አስታውቋል።

ይህንኑ ተግባር አስመልክቶ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ብቻ ምግብን ከባእድ ነገር ጋር ይቀላቅላሉ ተብሎ ከተጠረጠሩ 189 ምግብ አምራች ተቋማት ውስጥ 63ቱ በተግባሩ ውስጥ አሉ ተብለው ተጠርጥረዋል።

እነዚህ ተቋማት ምግብን ከባእድ ነገር ጋር በማቀላቀል ተጠርጣሪ የሚያደርጋቸው አመላካቾች የተገኙባቸው በመሆኑ ፍተሻና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ነው ወይዘሪት ሄራን የገለፁት።

ተቋማቱ ጤፍን ከጄሶና ከተፈጨ ሰጋቶራ ጋር በማደባለቅ የተጋገረ እንጀራ፣ በርበሬ፣ ማርና ቂቤን ከተለያዩና ምንነታቸው ከማይታወቅ ባእድ ነገር ጋር በመቀላቀል ለገበያ በማቅረብ የተጠረጠሩ መሆናቸውን አክለዋል።

የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ አለመኖር የሚያመርቱበት ሁኔታ እጅግ ጽዳቱን ያልጠበቀና ለምግብ ማምረቻነት ብቁ ያልሆነ መሆኑን እንዲሁ።

ተግባሩ በድብቅ፣ በሌሊትና ትክክለኛ አድራሻ በሌላቸው ቤቶች ውስጥ የሚሰራ በመሆኑ ኦፕሬሽኑን ውስብስብ እንዲሆን አድርጎት ነበር ያሉት ዳይሬክተሯ የተገኙት ምግቦች በላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።

ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድም የተቀላቀሉት ባእድ ነገሮች ምንነት በምርመራና በላብራቶሪ የማረጋገጥና በጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በመለየት የተሟላ መረጃ የማሰባሰብ ሂደት እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

የአዲስ አበባ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ወንድሙ በበኩላቸው በዚሁ ምግብን ከባእድ ነገር ጋር በመቀላቀል እጅ ከፍንጅ የተያዙ ግለሰቦችን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሂደት ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላይ አምስት እንጀራ የሚያዘጋጁ ግለሰቦች፣ ቦሌ ሶስት ግለሰቦች፣ አራዳ አራት ግለሰቦች ተቋማቸው እንዲታሸግና ፍርድ እስኪበየንባቸው በቁጥጥር ስር ውለው ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከንጽህና፣ ከጤና ምርመራና ከብቃት ማረጋገጫ ጋር በተያያዘ ያሉበትን ቁመና ማስተካከል ያለባቸው አምራቾች የተለዩ ሲሆን ማስተካከያ ያደረጉት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፤ ይህንን ያላሟሉት ደግሞ እስኪያሟሉ ድረሰ ተዘግተው ይቆያሉ ብለዋል። 

ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ ለምርመራ ወደ ላብራቶሪ የተላኩ ናሙናዎች የምርመራቸው ውጤት በወቅቱ ባለመድረሱና አጥፊዎችንም ለመቅጣት የሚያግዘው መረጃ ባለመሟላቱ የፍርድ ሂደቱ እንዲጓተት ማድረጉንም ገልፀዋል።

የተደራጀና ባእድ ነገርን የሚለይ ራሱን የቻለ የላብራቶሪ ማእከል በአገር ደረጃ ባለመኖሩ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ጫና እያሰደረ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም