የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኦሮሚያን የወከሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ አሸነፉ ቢባልም ምርጫው ድጋሚ እንዲካሄድ ተወስኗል። ዛሬ በአፋር ሰመራ በተካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ኦሮሚያ ክልልን የወከሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ 66 ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነው ነበር። ይሁንና በምርጫው መመሪያ መሰረት አቶ ኢሳያስ ከተሰጠው 145 ድምጽ አብላጫ ወይም 50 ሲደመር 1 ባለማግኘታቸው የፕሬዝዳንትነት ምርጫው ድጋሚ እንዲካሄድ የምርጫ አስመራጭ ኮሚቴው ወስኗል። ያገኙት ድምጽ ወደ መቶኛ ሲቀየር 46 ከመቶ በመሆኑ ነው ምርጫው እንዲደገም የተደረገው፡፡ የፕሬዝዳንትነቱም ሆነ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ከሰዓት በኋላ እንደሚካሄድ ታውቋል። በተሰረዘው ምርጫ አማራ ክልልን የወከሉት አቶ ተካ አስፋው 47፣ ድሬዳዋ ክልልን የወከሉት አቶ ጁነዲን ባሻህ 28 እንዲሁም የትግራይ ክልልን የወከሉት አቶ ተስፋዬ ካህሳይ 3 ድምጽ አግኝተዋል። የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ የእግር ኳስ ማህበራትና የዳኛ ማህበር የምርጫው ድምጽ ሰጪ አካላት ናቸው።