ቀጥታ፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከሰኞ ጀምሮ ስብሰባውን ያካሂዳል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ከሰኞ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል።

ምክር ቤቱ ከሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመልክቷል።

በዚሁ ስብሰባው አገራዊና ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ቀደም ሲል ምክር ቤቱ መስከረም 4 እና 5 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል።

በወቅቱ የምክር ቤቱ ስብሰባ ሲጠናቀቅ፤ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስማምቶ በመሄድ ረገድ የሚያጋጥሙ የአመለካከትም ይሁን መዋቅራዊ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ የለውጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ማስቀመጡ በመግለጫ መግለጹ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ ለህዝቡ የህግ የበላይነት እንዲከበር በፅናት እንዲታገልና ለውጡን ጠብቆ እንዲያስቀጥል ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም።

በአገሪቷ የተጀመረው ለውጡ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ይዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም  በውሳኔው ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሽ ነው።

የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ አገራዊ ዕድገቱን ለማስቀጠል የምርትና ምርታማነትን በቀጣይነት ማሻሻል አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥቶትም ነበር።

በመስከረሙ ስብሰባው የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ላይ የመከረው ምክር ቤቱ "ጽንሰ ሀሳቡ ... ህዝቡ በሙሉ ፍላጎቱ እንዲያውቀው፣ እንዲያሰፋውና የለውጥ መርሆዎቹን ተገንዝቦ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ" ለማድረግ እንዲችል የተለያዩ ተግባራት እንዲከናወኑ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።

የፖለቲካ ማሻሻያዎች የኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት፣ አስተዳደራዊ እና የህግ ሪፎርሞች የማካሄድ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም።

ጠንካራና መልካም የመንግስት አስተዳደር ለመፍጠር ያልተማከለና ለዘርፉ ልዩ ባህሪ ትኩረት በመስጠት የፍትህ ተቋማት፣ የምርጫ ቦርድና የደህንነት ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ምክር ቤቱ ከሰኞ ጀምሮ በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎቹ ያለፉት ወራት የድርጅቱ ሥራዎች አፈጻጸምን ይገመግማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም