አዲስ አበባ የአስፈጻሚ ተቋማትና የመንግስት ሰራተኞች ምደባ በአዲስ መልክ እያደራጀች ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የአስፈጻሚ ተቋማትና የመንግስት ሰራተኞች ምደባ በአዲስ መልክ እያደራጀች ነው
ሚያዚያ 4/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ ተቋማትንና የመንግስት ሰራተኞችን በብቃት ላይ በመመስረት በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየሰራሁ ነው አለ።
በአስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ነጂባ አክመል የከተማዋ አዲሱ አመራር ስራ ከጀመረ በኋላ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ወደ ሪፎርም መግባቱን ገልጸዋል።
ለተግባራዊነቱም የአስፈጻሚ ተቋማት ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል 400 አባላትና 16 አማካሪዎች ያሉት የጥናት ቡድን ዳሰሳ አድርጓል ነው ያሉት።
ጥናቱ የተቋማት የተግባርና ስልጣን መደራረብና ተመሳሳይነት፣ የስራ ባህሪና ተመጋጋቢነት፣ ግልጽነትን፣ የበጀት ቁጠባና ቁጥጥርን መሰረት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ለተገልጋዩ በአንድ ተቋም አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችልና የስልጣንና ተግባር መደራረብን ለመቅረፍ በሚያስችል ሁኔታ 63 ተቋማት እንደገና ተደራጅተዋል ነው ያሉት።
በቢሮው የኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተመስገን በበኩላቸው የተቋማት ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም የሰው ሃይል አደረጃጀት በጥናት ተለይቶ የሰራተኛ ድልድሉን እንደገና ለማካሄድ የምዘናና የምደባ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ መገባቱን ነው የገለፁት።
የሰራተኞች ምደባ ብቃትንና እውቀትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን የገለጹት አቶ መላኩ፤ ለዚህም ሰራተኞቹ ራሳቸውን በራሳቸው፣ በባልደረቦቻቸውና በሃላፊያቸው ተመዝነው ውጤቱ ወደ ማዕከል እንዲገባ አቅጣጫ መቀመጡን ነው ያነሱት።
ምዘናው ከስራ አፈጻጸም፣ ከስነምግባር፣ ግዴታን ከመወጣት፣ ከትምህርት ዝግጅት፣ ከማህደር ጥራትና ከስራ ልምድ አኳያ እያንዳንዱ ሰራተኛ ምን ይመስላል የሚለውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በስራ መደቦቹ ትክክለኛው የሰው ሃይል እንዲመደብ የሰራተኞች ግዴታንና ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት 65 በመቶ፣ የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ከ20 በመቶ፣ የማህደር ጥራት፣ የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ 15 በመቶ እንደሚይዝም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ነጂባ በበኩላቸው በሪፎርሙ በህብረተሰብ እርካታ 28 በመቶ የሆነውን አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለመቀየር የሰራተኞች አስተሳሰብ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።
አቶ መላኩ እንዳሉት የአሁኑ የሰው ሃይል ድልድል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የስራ ሂደት ለውጥ ጥናት ነው።
አሁን ተቋማት ሰራተኞቻቸውን እየመዘኑ እየላኩ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ሳምንት ሁሉም ተቋማት የተጠናቀቀ ውጤት ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ እንዲያስገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
የምዘናውን መጠናቀቅ ተከትሎ የሰራተኞችን ምደባ ለመጀመር ለየተቋማቱ የተፈቀዱ የስራ መደቦች፣ ደረጃ እና የተፈቀደ የሰው ሃይል ብዛት በመጪው ሳምንት እንደሚላክ ተናግረዋል።
በአሁኑ የሰው ኃይል ድልድል መምህራን፣ የጤና ጣቢያ፣ የሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሰልጣኞች አይካተቱም ተብሏል።
ከተጠቀሱት ባለሙያዎች ውጪ እስከ ከፍተኛው የሲቪል ሰርቪስ የስራ መደብ ዳይሬክተር ድረስ ባሉ መደቦች ከ90 ሺህ በላይ የሰው ሃይል እንደገና ይደለደላል ነው ያሉት።
ከተጣመሩ ወይም ከታጠፉ ተቋማት የሚቀነሱ ሰራተኞችም በሚመጥናቸው የስራ መደቦች ላይ ተወዳድረው በሌሎች ተቋማት ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።
ምደባውን ከፖለቲካዊና ከሃላፊዎች ጫና ነጻ ለማድረግ ክትትል ይደረጋል ያሉት አቶ መላኩ ሰራተኞች በውድድሩ የትምህርት ዝግጅታቸውና የስራ ልምዳቸው በሚፈቅድላቸው ሶስት የስራ መደብ በመምረጥ እንደሚያመልክቱም ገልጸዋል።
በዚህም ሰራተኞች ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያድጉ፣ ባሉበት ሊቀጥሉ ወይም ዝቅ ሊሉ የሚችሉ ቢሆንም ደረጃቸው ዝቅ ብሎ የሚመደቡ ሰራተኞች አሁን የያዙትን ደመወዝ ይዘው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የስራ ምደባ ሂደቱን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአስተዳደሩ ሰራተኞች በበኩላቸው መንግስት የጀመረው የለውጥ ስራ መልካም ቢሆንም የጥናቱ ትግበራ መዘግየት የስራ እንቅስቃሴ መፋዘዝን በማስከተሉ ደንበኞችን ለቅሬታ መዳረጉንና የነሱንም የሞራል ተነሳሽነት መቀነሱን ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ከግምት በማስገባት የስራ ምደባው ህጋዊነትን ጠብቆ በፍጥነት እንዲተገበርም ጠይቀዋል፡፡
ወይዘሮ ነጂባ በበኩላቸው የስራና ሰራተኞች ድልድሉ በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸው “የስራ መፋዘዝ ካለ መታረም ይገበዋል” ብለዋል።