ቀጥታ፡

የሶማሌ ክልል የህዝብ ግንኙነቱን የሚያሳድግ ጉባኤ ሊያከናውን መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011  የሶማሌ ክልልና ህዝብ ከአካባቢው ባለፈ ለአገራዊ አንድነቱ ቀናኢ መሆኑን ለማሳየት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ መሃመድ ኡመር ተናገሩ ።

የሶማሌ ክልል ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በቀጣይ ከሌሎች ክልሎች ጋርም በአንድነት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በነገው እለትም ድሬዳዋ ላይ የአፋር፣ ኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎችን አንድ ላይ በመድረክ የሚያመጣ ጉባኤ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጨምረው እንደገለጹት፤ በ2010 ዓ.ም ሃምሌ ወር መጨረሻ ላይ በጅግጅጋ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

የክልሉ አመራር ከሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ጋር በመነጋገር የተፈጠረው ችግር ህዝቡን የማይወክል መሆኑንና ይህን ተከትሎ የተፈጠሩ አንዳንድ ስሜቶች መርገብ እንዳለባቸው ከመግባባት መድረሳቸውንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ አጎራባች ህዝቦች ጋር ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱንና የሰላም ሁኔታውም ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱንም ተናግረዋል።

ከአንዳንድ ውስን ቦታዎች በስተቀር በአብዛኛው ህዝብ ማህበራዊ ትስስሩን በድጋሚ መጀመሩንም እንዲሁ።

ጉባኤው እስከ አሁን በመንግስት ደረጃ የተሰሩትን ስራዎች እንደሚያሳድጋቸው እምነታቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ የመንግስት መዋቅር ማሻሻያ መደረጉንና በፓርቲ ደረጃም የተካሄደው ጉባኤ አዲስ፣ የተማረና የጸጥታ ሁኔታውን የሚያስከብር ኃይል ለማውጣት ማስቻሉንም ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በፖለቲካው፣ በጸጥታና በመንግስት መዋቅር በኩል ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል።

በለውጡ በመታገዝ ክልሉ እንደ አዲስ እንደተወለደና የተረጋጋ ሰላም የሰፈነበት አካባቢ ለመሆን መብቃቱንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም