የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር ውድድር የተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነትና የተመልካች ቁጥር የታየበት ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር ውድድር የተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነትና የተመልካች ቁጥር የታየበት ነው ተባለ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 የመጀመሪያ ዙር የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነትና የተመልካች ቁጥር የታየበት እንደሆነ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የ2011 ዓ.ም የሐበሻ ሲሚንቶ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር ውድድር አፈጻጸምን ገምግሟል።
የፕሪሚየር ሊጉ የአንደኛ ዙር ውድድር ከህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የተካሄደ ሲሆን ስምንት ክለቦች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቮሊቦል ስፖርት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ተፈራ በላቸው የአንደኛው ዙር ውድድር በአመዛኙ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ መካሄዱን ገልጸዋል።
በባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር የዳኛን ውሳኔ ያለመቀበል፣ ዳኛን የክለቡ አምበል ሄዶ ማናገር እየተገባው ተጫዋቾች መመሪያ በጣሰ መልኩ ግር ብለው በመሄድ የሚቃወሙበት ሁኔታ እንደነበር አውስተዋል።
አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች የዳኞች ውሳኔን ስፖርታዊ ጨዋነት በጎደለው መልኩ ይቃወሙ እንደነበርም ገልጸዋል።
የዘንድሮው ውድድር ከመካሄዱ በፊት ከክለቦች ጋር በተደረገ የቅድመ ውድድር ስብሰባ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሩን ለመፍታት በተቀመጠው የጋራ አቅጣጫ አንደኛው ዙር የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት የተላበሰ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይሄም መልካም ተግባር በሁለተኛው ዙር ውድድር እንዲቀጥልም ክለቦች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባዋል ብለዋል።
የመከላከያ ቮሊቦል ስፖርት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ተከተል ሙጎሮ በበኩላቸው በአንደኛ ዙር በተካሄዱ ጨዋታዎች ውድድሩን የሚከታተሉ ተመልካቾች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰዋል።
በክለቦች መካከል ያለው ፉክክር ተመጣጣኝ እንደነበረ ገልጸው የመርሃ ግብሮች በተወሰነ መልኩ መቆራረጥ በቀጣይ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል። በዳኞች ላይ ያለው የአቅም ክፍተት መፈታት እንዳለበትም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴ አባል አቶ ንጉሴ አለሙ የስፖርታዊ ጨዋነቱ መሻሻል ቢያሳይም ተጫዋቾች በምልክትና በአፍ የመሳደብ ሁኔታና የዳኞችን ውሳኔ የመቃወም ነገር ሊታረም እንደሚገባው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ የ2011 ዓ.ም ውድድር በፊት ከክለቦች ጋር በመሆን የተደረጉት የቅድመ ዝግጅትና የቅንጅት ስራዎች ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ ለማካሄድ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊጉን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት መሰራቱና የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲያገኝ የተሰራው ስራ ውድድሩ የተሻለ የተመልካች ቁጥር እንዲያስተናግድ ማድረጉን ገልጸዋል።
የስፖርታዊ ጨዋነት በተመለከተ ከክለቦች ጋር ከተደረገው ውይይት በተጨማሪ የስነ ምግባር ጉድለት በፈጸሙ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ላይ የቅጣት እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
የውድድር ቀናት መቀያየር፣ በውድድር ሜዳዎች ጥበት ምክንያት ተመልካችና ተጫዋቾች በጣም መቀራረባቸው ለተጫዋቾች ደህንነት ስጋት መሆኑ፣ በአንዳንድ ጨዋታዎች የጸጥታ አካላት አለመሟላትና ሜዳዎች በሌሎች ውድድሮች መያዛቸው እንደ ችግር አንስተዋል።
ችግሮቹን በመፍታት በሁለተኛው ዙር የተሻለ ውድድር ለማድረግ ክለቦችም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የሁለተኛ ዙር የ2011 ዓ.ም የሐበሻ ሲሚንቶ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ውድደር ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚጀምር በግምገማው ወቅት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የተለያዩ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች፣ ዳኞች፣ አሰልጣኞችና ባለድርሻ አካላት በግምገማው ላይ ተሳትፈዋል።