ቀጥታ፡

በፓርኩ እየደረሰ ያለውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮች ከውጪ አገሮች ሊመጡ ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ እየደረሰ ያለውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት የሚረዱ ሄሊኮፕተሮች ከውጭ አገሮች እንደሚመጡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ሄሊኮፕተሮቹን ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ እና ከፈረንሳይ ለማስመጣት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን አገሮቹም ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል ተብሏል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፤ ከሳምንታት በፊት በፓርኩ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋትና ፓርኩን ለመታደግ ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

በተለይም የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች በገንዘብና በጉልበት ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ እየደረሰ ያለውን ቃጠሎ ለማስቆምና የፓርኩን ህልውና ለመጠበቅ በቴክኖሎጂ መታገዝ አስፈላጊ ሆኗል።

ይሁንና ኢትዮጵያ እንደነዚህ ያሉ ድንገተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አቅም የሌላት በመሆኑ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮችን ከውጭ አገሮች የሚመጡ ይሆናሉ ብለዋል።

በዚህም የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት የሚረዱ ሄሊኮፕተሮችን ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ እና ከፈረንሳይ ለማስመጣት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቃጠሎው ይበልጥ እንዳይስፋፋና ወደ ገደላማው የፓርኩ ክፍል የገባውን እሳት ለመቆጣጠርም እስከ ስድስት ሄሊኮፕተሮች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

ሄሊኮፕተሮቹ የእሳት ቃጠሎው ቶሎ እንዲጠፋና ወደ ደኖች እንዳይስፋፋ የሚያግዙ በመሆናቸው በአፋጣኝ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና መፍትሄ እንሚሰጠውም ተናግረዋል።

ፓርኩ ባጋጠመው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት እስካሁን በትላልቅ አጥቢ እንስሳት ላይ በዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ በቀይ ቀበሮና በሌሎችም ላይ የሞት አደጋ አለመድረሱን አክለዋል።

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአጠቃላይ ወደ 412 ኪሎ ሜትር ስኩየር የሚሸፍን ሲሆን በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማወቅም በባለሙያዎች ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝና በቅርቡ ይፋ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም