ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2011 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
ገቢው የተገኘው ከስድስት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድና ከልዩ ልዩ ገቢዎች መሆኑም ታውቋል።
ኢንተርፕራይዙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው በተያዘው በጀት ዓመት ዘመናዊ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት በመጠቀም ለክፍያ መንገድ ተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 6 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ ከ191 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ገቢዎችም 13 ሚሊዮን በአጠቃላይ ከ204 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ነው የገለጸው።
እንደ ኢንተርፕራይዙ መረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአዲስ አዳማን የፍጥነት መንገድ ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮች ተከናውነዋል። በመንገዱ ክልል ውስጥም የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሰርቷል።
የመንገዶች የጥገና አቅምን በማሳደግ በአገልግሎት እድሜ ማብቃትና በአደጋ ምክንያት በንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በአፋጣኝ በመጠገን የመንገዱ ምቾት እንዳይጓደል እየሰራ መሆኑንም ነው ያመለከተው።
የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ፣ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያና የደንበኞች የጥሪ ማዕከል ግንባታ፣ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት ማሻሻያ እንዲሁም የስራ ቦታን ምቹ ማድረግ ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ተግባራት ናቸው።
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸዉ የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ እንዲሁም በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት በሚፈለገው መጠን መቀነስ አለመቻል ደግሞ በኢንተርፕራይዙ ያጋጠሙ ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል።