መኢአድ አዳዲስ የአመራር አባላትን መረጠ - ኢዜአ አማርኛ
መኢአድ አዳዲስ የአመራር አባላትን መረጠ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አዳዲስ የአመራር አባላትን መረጠ።
መኢአድ ከመጋቢት 28 እስከ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባካሄደው የድርጅቱ 8ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ አዳዲስ የአመራር አባላትን በመምረጥ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የፓርቲው አመራር አባላት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ጠቅላላ ጉባኤው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይ በተገኙበት የአዳዲስ አመራር አባላት ምርጫ አካሂዷል።
በዚህ መሰረት ላለፈው ሁለት ዓመት ከአስር ወር ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩት በቆዩት ዶክተር በዛብህ ደምስ ቦታ አቶ ማሙሸት አማረ የተተኩ ሲሆን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ደግሞ አቶ አብርሃም ጌጡ ሆነው ተመርጠዋል።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ባሉበት ቦታ እንዲቀጥሉ ጠቅላላ ጉባኤው መመረጣቸው ተገልጿል።
የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ከማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ውስጥ 20 የስራ አስፈፃሚ አባላትን አቅርበው በጠቅላላ ጉባኤው የፀደቀላቸው መሆኑን እና የአመራር እና የማዕከላዊ ሥራ አስፈፃሚ አባላትን ጨምሮ 105 የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን በመምረጥ ጉባኤው መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ፓርቲው በፕሮግራምና በሀሳብ ከሚመስሉት ሌሎች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጥምረትና በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።