ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ወጣቱ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል--- አባት አርበኞች

66
ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 30/2010 ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ወጣቱ አንድነቱን በማጠናከር የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አስታወቀ። በደብረ ብርሃን ከተማ 77ኛው የአርበኞች የድል በዓል በተለያዩ ስነ ስርአቶች ትናንት ተከብሯል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳኔኤል ጆቴ መስፍን በበዓሉ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ወጣቱ ከጀግኖች አርበኞች የተረከባትን ሀገር አንድነቷን በመጠበቅ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የላቀ ሚናውን ሊወጣ ይገባል። በዘር፣ በብሔርና በሃይማኖት ሳይከፋፈል የቀድሞ የአባቶቹን ታሪክ በመዘከርና አንድነቱን በማጠናከር ለተሻለ እድገት መትጋት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። "ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና እርስ በእርስ መግባባትን መፍጠር ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅ አቅም ይፈጥራል" ብለዋል ። የሰሜን ሽዋ ዞን አርበኞች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋስላሴ ከበደ በበኩላቸው "ጀግኖች አርበኞች ለሃገራቸው ክብር ሲሉ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ በርካቶችም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል " ብለዋል። ወጣቱ ከአባት አርበኞች የተረከባትን ሀገር አንድነቷን አጠናክሮ የማስቀጠል ኃላፊቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዘበዋል። ሀገሩን የሚወድና ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር የሁሉም አካል የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ተስፋስላሴ ጠቁመዋል። አባት አርበኛ አቶ ብዙወርቅ ጎርፌ በበኩላቸው "ወጣቱ ዳር ድንበሯ የተከበረች ሀገር ያስረከቡትን አባቶች መንከባከብ፣ መደገፍና ታሪክ መጠበቅ አለበት " ብለዋል ። በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ሀብታሙ መኮንን "የሴት አርበኞች ሚና በጣሊያን ወረራ" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል ። ሀገሪቱ በመጣችባቸው ታሪኮች የሴት አርበኞች ድርሻ ምን እንደሆነ በጽሁፋቸው አሳይተዋል። በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ቸርነት ወኔ በበኩሉ "አባቶች ያስረከቡንን ሀገር በመጠበቅ ከድህነትንና ኋላቀርነት ለማላቀቅ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የድርሻዬን እወጣለሁ" ብላል ። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና በሰሜን ሽዋ ዞን አርበኞች ጽህፈት ቤት ትብብር በተዘጋጀው በዓል ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም