በመቀሌ የተበላሹ ትራንስፎርመሮችን ጠግኖ ጥቅም ላይ ለማዋል የተከፈተው ማዕከል ሥራ ጀመረ

መቀሌ ሚያዚያ 3/2011 በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በመቀሌ ከተማ የተከፈተው የጥገና ማዕከል ሥራ ጀመረ። 

የጥገና ማዕከሉ የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የትግራይ ክልላዊ መንግስት በመደቡት 50 ሚሊዮን ብር በጀት ነው።

የጥገና ማዕከሉ በትግራይ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮችን ጠግኖ መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ለኢዜአ እንዳሉት፣ የማዕከሉ መከፈት በክልሉ ያለውን የትራንስፎርመር አቅርቦት ችግር ለመፍታት እገዛው የጎላ ነው።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞች በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ከ700 በላይ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች ይገኛሉ።

አነስተኛ፣መካከለኛ እና ትላልቅ ተብለው ከተለዩ ትራንስፎርመሮች መካከል 300 የሚሆኑት በዘንድሮ ዓመት ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ማዕከሉ ወደስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 42 ሚሊዮን ብር በጀት የመደበ ሲሆን፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስትም 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ መስፍን አስታውቀዋል።

ማዕከሉ በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ሥራውን የጀመረ ሲሆን ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥም ከ100 በላይ የተበላሹ ትራንስፎርመሮችን ጠግኖ ለመብራት፣ ለመጠጥ ውሃ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለጤናና ለትምህርት ተቋማት አገልግሎት ማብቃቱን ገልጸዋል።

በቀጣይ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ 200 የሚሆኑ ትራንስፎርመሮች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።

በቀጣይ ዓመትም ከ400 በላይ የተበላሹ ትራንስፎርመሮች የጉዳታቸውን መጠን የመለየትና የመጠገን ሥራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በተጠገኑ ትራንስፎርመሮች ተጠቃሚ ከሆኑ የሕብረተስብ ክፍሎች መካከል በትግራይ ደቡባዊ ዞን ራያ ዓዘቦ ወረዳ ክክፍቶ ገጠር ቀበሌ በዘመናዊ የመስኖ ልማት ሥራ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ኢብራሂም ያሲን አንዱ ናቸው።

በትራንስፎርመር አቅርቦት ችግር ምክንያት ለሰባት ዓመታት ያህል የመስኖ ልማት ሥራውን በዘመናዊ መልክ ለማከናወን ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በየዓመቱ ከመስኖ ማግኘት የነበረባቸው 100 ሺህ ብር የሚገመት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በችግሩ ምክንያት ማጣታቸውን ባለሃብቱ አስታውሰው፣ የጥገና ማዕከሉ የትራንስፎርሞር ጥያቄያቸውን መመለሱን ተናግረዋል።

ባለሃብቱ ባገኙት ትራንስፎርመር በአካባቢው የሚገኙ 50 አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓዲግራት ከተማ በዕንጨትና ብረታብረት የሥራ ዘርፍ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ዮናስ ተስፋይ በበኩሉ በከተማው የትራንስፎርመር አቅርቦት ባለመኖሩ ለአራት ዓመታት ያህል ተቸግረው መቆየታቸውን ገልጿል።

ችግራቸው ከአንድ ወር በፊት በመፈታቱ  በአሁኑ ወቅት የብረታ ብረትና የዕንጨት ምርቶችን በተሻለ ሁኔታ ለማምረት መቻላቸውን አመልክተዋል።

ማዕከሉ የሚስተዋለውን የትራንስፎርመር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም