የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ባለፈው አንድ አመት የመጣውን አገራዊ ለውጥ እንደሚያደንቅ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ባለፈው አንድ አመት የመጣውን አገራዊ ለውጥ እንደሚያደንቅ ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 2 /2011 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ባለፈው አንድ አመት የመጣውን አገራዊ ለውጥ እንደሚያደንቅ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ብሔራዊ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ሰላም መስፈንና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር በጋራ መስራት እንዳለባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርቧል።
“ከመጋቢት እስከ መጋቢት” አዲሱ አመራር ያመጣቸውን ለውጦች የሚደግፍ መሆኑን ያስታወቀው ማህበሩ በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ተናበው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝቧል።
ባለፈው አንድ ዓመት የሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት፣ የሚዲያ ነፃነት፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታትና ከአገር ውጭ ሆነው ለአገራቸው ፍትህ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት እንዲገቡ መደረጉን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪስ መሀመድ ገልጸዋል።
ለሃያ ዓመታት ተለያይቶ የቆየው የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስትና ህዝብ ግንኙነት እንዲፈጠር መደረጉ ዳያስፖራውን ለአገሩ እንዲቆም በመንግስት በኩል የተሰራውን ስራ ማህበሩ እንደሚያደንቅ ገልፀዋል።
''መንግስት ሠላምን ለማስጠበቅ አቋም አለመውሰዱ ዲያስፖራው ለአገሩ እንዳይቆም ያደርገዋል'' ያሉት አቶ እንድሪስ አገር ሰላም ስትሆን ዲያስፖራው ከያለበት የተሻለ ነገር ለአገሩ ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
የማህበሩ አባላት በጤናው ዘርፍ በቅርቡ የአይን ህክምና በመስጠት በተለያየ ችግር የአይን ብርሃናቸውን አጥተው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲያዩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የተጀመረው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ “አንድ ዶላር ከአንድ ቡና” እና በቅርቡ ተቀዛቅዞ የነበረው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገውን ድጋፍ አባላቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሠራ መሆኑን ተገልጿል።
በአንዳንድ አከባቢዎች የሚታየው የሠላም መደፍረስ ለውጡን ተከትሎ የመጣ ቢሆንም ኢህአዴግ በአባላቱ መካከል አንድነት ፈጥሮ ሰላም ለማስፈን መንቀሳቀስ ይገባዋል ብለዋል።
በአገሪቱ ሠላም ሲሰፍን ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በጤናና በዲፕሎማሲ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ለአገሪቱ እድገት የሚሰራበት ዕድል እንደሚሰፋ አቶ እንድሪስ ገልጸዋል።
መንግስት የአገርን ሰላም ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
የዲያስፖራ ማህበሩ በሰባት ዓመታት ጉዞው 15 ሺህ ቋሚ አባላት እንዲሁም አደረጃጀቱን በክልልና በከተማ አስተዳደሮች እንደዘረጋ ተገልጿል።