ኢትዮጵያ የነጻ የንግድ ቀጠና መስራች መሆኗ በውሳኔ ሰጪነት ላይ የራሷን ሚና እንድታበረክት ያስችላታል ተባለ

78

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና መስራች መሆኗ በውሳኔ ሰጭነት ላይ የራሷን ሚና እንድታበረክት ያስችላታል ተባለ።

ኢትዮጵያ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀችውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ሰነድ ለአፍሪካ ህብረት ዛሬ አስረክባለች።

እስካሁን ባለው ሂደት 51 የአፍሪካ አገሮች ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 22 የሚሆኑት ስምምነቱን በፓርላማቸው አጸድቀዋል።

ነጻ የንግድ ቀጠና ስርዓቱ እንዲተገበር 22 አገሮች የስምምነት ሰነዳቸውን ለአፍሪካ ህብረት ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል።

ከህብረቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 19 አገሮች በየፓርላማቸው ያጸደቁበትን የስምምነት ሰነድ ለህብረቱ ገቢ አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ የስምምነት ሰነዱን ለአፍሪካ ህብረት ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ የስርዓቱ ገቢራዊነት በኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ ከወጪ ንግዷ ውስጥ ወደ አፍሪካ አገሮች የምትልከው ድርሻ 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ለአብነት አንስተው፤ ''ይህም በአህጉሩ ያልተጠቀምንበት የገበያ እድል እንዳለ ያሳያል'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ የስምምነቱ መስራች አገር መሆኗ የነጻ ንግድ ስርዓቱ ምን መልክ መያዝ እንዳለበት በሚደረግ ውሳኔ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሚያደርጋትም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ስምምነቱን በመስራች ደረጃ ማጽደቋ አገሪቱ በዘመናት መካከል ለአፍሪካ አንድነትና ትስስር የማይለወጥ አቋም እንዳላት እንደሚያሳይም አቶ ማሞ አብራርተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሞቻንጋ በበኩላቸው ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጣና ስርዓቱ በቀጣይ ሐምሌ ወር በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ስምምነቱን በፓርላማቸው አጽድቀው ለህብረቱ ማስረከብ የቻሉ አገሮች ብቻ የነጻ ንግድ ስርዓቱ ተጠቃሚ እንሚሆኑም አውስተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅን ያጸደቀው ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ጉባኤ መሆኑ ይታወቃል።

ነጻ የንግድ ቀጠናው ወደስራ ሲገባ ለአንድ ቢሊዮን ሰዎች ያህል የገበያ ተደራሽ ከመሆን ባለፈ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ የአገር ውስጥ ምርት ግብይት የሚካሄድበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ነጻ የንግድ ቀጣናው ወደተግባር ሲገባ አህጉራዊ የንግድ ውድድርን በማጠናከር፣ የስራ ዕድልን በማስፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አህጉራዊ የንግድ መዳረሻን በማስፋፋት ረገድ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም