ድርቅን የሚቋቋሙ ሃገር በቀል አትክልትና ፍራፍሬ ዝሪያዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ድርቅን የሚቋቋሙ ሃገር በቀል አትክልትና ፍራፍሬ ዝሪያዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ሶዶ ሚያዝያ 2/2011 ድርቅን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ በመድረስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚችሉ ሃገር በቀል የአትክልትና ፍራፍሬ ዝሪያዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸራል ሳይንስ ሶሳይቲ ማህበር ያዘጋጀው ሰባተኛው የምርምር ኮንፈረንስ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በኮንፍረንሱ ከተሳተፉት መካከል ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የመጡት አቶ ነኢም ሰማን በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ያሉ የእንሰት ዝሪያዎችን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
"እንሰት ከፍተኛ የሆነ ብረት የተባለና የአልሚ ምግብ ንጥረ ነገር፣ ውሃን የመያዝ ተፈጥሮዊ አቅም ያለው በመሆኑ የዝናብ እጥረት የማያሰጋው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የተክል ዝሪያ ነው "ብለዋል፡፡
ቀዝቃዛ አየር በመሳብ የተፈጥሮ ሚዛኑን ለመጠበቅና በሽታን ለመከላከል ያለው ተፈጥሮዊ አቅም ከፍተኛ ቢሆንም ዝሪያውን ከመጠበቅ አንጻር ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡
በአብዘኛው በደቡብ ክልል ሚገኘው እንሰት ዝርያውን ጠብቆ ለመጠቀም የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ከመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሆርቲ ካልቸር ተመራማሪ ዶክተር ኢዶሳ እዴሳ በበኩላቸው "በምግብና በመድኃኒትነት ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ላም አተርና ዱባ ቅጠል የመሳሰሉ ሰብሎች ትኩረት አልተሰጣቸውም"ብለዋል፡፡
የምግብ ዕጥረት ችግር ሊያቃልሉ የሚችሉ እነዚህና ሌሎችም ዝርያዎች በግብርና ኤክስቴንሽን ማግዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አትክልትና ፍራፍሬን በተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተከትሎ በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑት በቂ ባይሆንም ውጤት እያመጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ፕሮፌሰር ተረፈ በልሁ ናቸው፡፡
የምግብ ደህንነትን ሊያረጋግጥ የሚችል በእጅ ያለ ሃብት ለመጠቀም ትኩረትና የቅንጅት ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከተመራማሪዎች የሚቀርበውን ምክረ ሃሳብ ውጤታማ ለማድረግ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በግብርና ኤክስተንሽን የአተገባበር የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀትና ወደአርሶ አደሩ ለማውረድ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር መስፍን ቢቢሶ ኮንፍረንሱ በጠባብ መሬት የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ ምርታማ ለሆኑ አትክልቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው አቅጣጫ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸራል ሳይንስ ሶሳይቲ ፕረዝዳንት ዶክተር አዱኛ ደበላ ማህበሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨትና ማስተዋወቅ እንዲሁም የምርምር ስራዎችን በመለየት ለማዳረስ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ ፣ ቡና፣ አበባ፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም ሃገር በቀል ዝሪያዎች ላይ ለመስራት ትኩረት መስጠታቸውን አመልክተው ዘንድሮ ከምግብ ደህንነት ጋር በማገናኘት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ለመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የግብርና ምርምር ማዕከላት የተወጣጡ ተመራማሪዎች በተሳተፉበት ኮንፈራንሱ ከ20 በላይ የምርምር ስራዎች ቀርበዋል፡፡