ቀጥታ፡

በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የመታሰቢያ መርሃ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ 33 የተባበሩት መንግሥታትና የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች የመታሰቢያ መርሃ-ግብር ተካሄደ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው መርሃ-ግብር ለሟች ሠራተኞች በተለያዩ የእምነት አባቶች የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

የተ.መ.ድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ቬራ ሶንግዌ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የደረሰው አደጋ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ የሟች ቤተሰቦችም አሁን ያሉበት ጊዜ በጣም ከባድ ነው። 

ይሁንና ዛሬ በተዘጋጀው መርሃ-ግብር የተቋማቸው ሠራተኞች ከሟች ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሃዘናቸውን እየተጋሩ መሆኑን ገልጸው ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናት ተመኝተዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሟች ቤተሰቦች ያደረገው እገዛ የሚደነቅ መሆኑንና ተቋማቸው ለሟች ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ መንግሥት በመወከል ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትና ጥንካሬን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ከሟች ቤተሰቦች ጎን እንደሚቆም ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ መውደቁ ይታወሳል።

በአደጋው 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በቅርቡም የአውሮፕላኑ የመረጃ ሣጥን /ብላክ ቦክስ/ በፈረንሳይ አገር ከተመረመረ በኋላ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሥሪት ላይ ችግር መኖሩ ተረጋግጧል።

የቦይንግ ኩባንያም በመርማሪ ቡድኑ የወጣውን መረጃ በመቀበል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ይቅርታ ጠይቆ ለሟቾች ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል።

ያም ሆኖ በፈረንሳይ አገር በምርመራ ላይ የሚገኘው የመረጃ ሣጥን ሙሉ መረጃ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም