ቀጥታ፡

የህዝብ ጥያቄዎች ሁነኛ ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት ያለመታከት ይሰራል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2010 በተለያዩ ጊዜያት የህዝብ ጥያቄ ሆነው የቆዩት ጉዳዮች ሁነኛ ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት ያለመታከት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ ማምሻው መግለጫ ሰጥተዋል። ከችግሮቹ ስፋትና ጥልቀት አንጻር ህዝብ በሚፈልገው ልክና መጠን ለሁሉም ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም መንግሥት የመጨረሻውን የፍጥነትና የትጋት ልክ ተጠቅሞ “ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ነገሮች ሁሉ መልካም እንዲሆኑ ከህዝቡ ጋር ይረባረባል” ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባጋጠማት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲታወጅ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል። ይህን ተከትሎ በመንግሥት በተከናወነው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርና በተከታታይ በተወሰዱ እርምጃዎች መንግሥት ባለው ችግሮችን የመፍታት ፍላጎትና አቅም ላይ ህዝቡ ተስፋ መሰነቁን ገልጸው፤ በዚህ ምክንያት ህዝቡ እራሱ የሰላሙ ዘብ በመሆን ላለፉት ሁለት ወራት በአገሪቱ አንፃራዊ የሰላም ነፋስ መንፈስ መጀመሩን ተናግረዋል። በመሆኑም "መንግሥት ህዝብንና ህዝብን ብቻ አምኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ህዝባችንም በአገሩ ምድር ሁሉ ላይ የሁሌም የሚሆነውንና ከየሰው አዕምሮ የሚመነጨውን ተፈጥሯዊ የሰላም አዋጁን በኅብረት እንደሚያውጅ እምነቴ የጸና ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ትናንቱን ዘክሮ፣ ዛሬውን መርምሮና ነገውንም ተንብዮ አገር አድባሩን በሰላም የሚሞላ ህዝብ ላላት ድንቅ ሀገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከቆየችው በላይ ትቆይ ዘንድ አይገባትም" ሲሉም የአዋጁን መነሳት አስፈላጊነት አስምረውበታል። መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለማንሳትና ህዝቡንም ወደ መደበኛው የአስተዳደር፣ የህግና የፍትህ መስመር ስለመመለስ ሲያስብ አዋጁን ለማወጅ ካስገደዱት ተግዳሮቶች አንፃር ያለውን ችግር በተመለከተ የመፍትሄውን ቁልፍ በማግኘት በኩል ሙሉ እምነቱ ያለው በህዝቡና በህዝቡ ላይ ብቻ እንደሆነም ግልጽ አድርገዋል። ከምንም በላይ ለዚህች ሀገር ብልጽግና እና ለህዝቦቿም ሰላም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ በጋራ እንዲረባረብም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ አቅርበዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙሉ መግለጫ ይህንን ሊንክ ተጭነው ያገኙታል.....
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም