ቀጥታ፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚሰሩ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ያለመ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 አሜሪካ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚሰሩ ተቋማት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች።

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ምክትል የአስተዳደር ኃላፊ ሚስ ቦኒ ግሊክ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እና የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፕሮጀክቱን ይፋ አድርገዋል።

"ፍትህ" የሚል ስያሜ ያለው ይህ ፕሮጀክት ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ስራዎች አጠቃላይ አራት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግ ሲሆን የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት/ዩ ኤስ ኤይድ/ የፕሮጀክቱን ወጪ ይሸፍናል።

በፕሮጀክቱ አማካኝነት ድርጅቱ ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለልተኛ ውሳኔ ሰጪነት እንዲኖራቸው እና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በጠቅላይ አቃቤ ህግ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መስኮች የህግ ማሻሻያዎች እያደረጉና አዲስ ህጎችን እያረቀቁ ላሉ ዳይሬክቶሬቶች፣ የስራ ክፍሎችና ቡድኖች የቴክኒክ ድጋፍ ይደረጋል።

የተራድኦ ድርጅቱ ለፍትህ መረጋገጥ ለሚሰሩ የሲቪክ ተቋማትም ድጋፍ በማድረግ የህግ የበላይነት በማስከበር ረገድ የሚሰሩ ስራዎችን ያግዛሉ ተብሏል።

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ምክትል የአስተዳደር ኃላፊ ሚስ ቦኒ ግሊክ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የተቀረጸው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ የለውጡ ስራዎችን ለመደገፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ የህግ የበላይነት የሰፈነበትና የዴሞክራሲ ባህል የዳበረበት አገር እንደሚፈልግና ይህም እንደሚገባው ገልጸው ለዚህም ካለምንም ተጽእኖ ውሳኔ መስጠት የሚችሉና አቅማቸው የተጠናከረ የፍትህ ተቋማት ያስፈልጋሉ ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስትም ለዚህ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ቁልፍ የሚባሉ የፍትህ ተቋማትም ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲሰጡ አስተዋጽኦ ማድረግ ከፕሮጀክቶቹ ዓላማዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ አማካኝነት ዜጎች በፍርድ ቤቶች ውጤታማና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

ለዚህም ከዓመት ዓመት የሚተላለፉ ውዝፍ መዝገቦችን በመቀነስ፣ ለዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ የዳኞችን አቅም የሚለካ የምዘና ስርዓት መዘርጋትና የዳኞች፣ የአስተዳደርና የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የተመለከቱ ህጎችም ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።

ዳኞች ለፍርድ ቤት ጉዳዮች የሚጠቀሙባቸውን የህግ መጽሐፎችም ወቅቱ ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ጠቁመዋል።

በፕሮጀክቱ የሚደረገው ድጋፍ በፍትህ ስርዓቱ እየተደረገ ያለውን ማሻሻያ እንደሚያግዝ ገልጸው በቀጣይም የአሜሪካ መንግስት የጀመረውን የመነሻ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለልማትና ለሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም