ቀጥታ፡

ቦርዱ ገለልተኛነቴን ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው አለ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ገለልተኛ መሆኔን ለማረጋገጥ ማሻሻያዎች እያደረግሁ ነው አለ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርትኳን ሚደቅሳ እንዳሉት የቦርዱን ገለልተኝነት እስከ ወረዳ ለማረጋገጥ የህግ ማሻሻያ ላይ ትኩረት ተደርጓል።

ከተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ውስጥ በቅርብ ቀን በፓርላማ የጸደቀውን በመጥቀስ በምርጫ አስፈጻሚነት ምልመላና ስልጠና ሂደት በግልጽነትና ሙያን መሰረት ባደረገ እንዲከናወን ጥናቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

"ማድረግ ያለብን ማሻሻያ የተጠጋገነ ሳይሆን በፊት ከነበረን በጣም የተለየ መሆን ስላለበት ነው" ሲሉ የተሰጠውን ትኩረት አብራርተዋል።

እንደ ሰብሳቢዋ ገለጻ ቀደም ሲል ምርጫው በሚፈጸምበት የምርጫ ጣቢያ ይሳተፉ የነበሩ አስፈጻሚዎች አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አባላት በመሆናቸው አቤቱታ ይቀርብ ነበር።

ይህን ለማስቀረት በቀጣዩ ምርጫ ገዥና ተፎካካሪ ሳይባል በየአካባቢው አመኔታ የሚያገኙ አስፈጻሚዎች አቅማቸውንና የሚሰጣቸውን ስልጠና ተቀብለው በትክክል መፈጸም የሚችሉ ዜጎችን ለመመልመል ከሌሎችም አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ እየተጠና ነው ብለዋል።

የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተም የአካባቢ እና የማጠቃለያ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ የመወሰንና ለህዝብ የማሳወቅ ስልጣን የቦርዱ መሆኑን ወይዘሪት ብርትኳን ተናግረዋል።

ሆኖም በህገ-መንግስቱና በሌሎች ህጎች የተቀመጡ የጊዜ ሁኔታዎችን ምርጫ ቦርድ የመቀየር ስልጣን እንደሌለው ገልጸው "ምርጫ ለማድረግ ያህል አናደርግም" ብለዋል።

ምርጫ የተሻለ ሁኔታ ለማምጣት መደረግ እንዳለበት የተናገሩት ሰብሳቢዋ እስካሁን ከተደረጉ ምርጫዎች የተሻለና በህብረተሰቡ ተአማኒ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዝግጅቱ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድና በኢትዮጵያ ያለው የሰላም ሁኔታ ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑም ይገመገማል ብለዋል።

"በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ማድረግ አንችልም ብለን የምናምን ከሆነ በዝርዝር በማስቀመጥ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ እናቀርባለን" ነው ያሉት። 

በ2012 በሚካሄደው ምርጫ የቦርዱን ገለልተኝነትና ተአማኒነት ለማረጋገጥ የማቋቋሚያ አዋጁንና የምርጫ ህጉን ማሻሻል እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም