ቀጥታ፡

የሲቪክ ማህበራት የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እንዲያደርጉ ምርጫ ቦርድ ጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2011 ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው በምርጫ እንዲሳተፉ የሲቪክ ማህበራት ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠየቀ።

ይህ የተባለው ምርጫ ቦርድ ከሲቪክ ማህበራት ጋር በስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ማኑዋል ረቂቅ ዙሪያ ምክክር ዛሬ ሲያደርግ ነው።

የማኑዋሉ አላማ ዜጎች መብቶቻቸውን አውቀው የሚጠቅማቸውንና የሚጎዳቸውን ያለማንም ጫና በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ ለማስተማር የተዘጋጀ ነው።

ማንዋሉን ቀደም ሲል ከነበረው የሚለይበትን ያብራሩት የማኑዋሉ አዘጋጅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ማኑዋሉ ዜጎች መራጭና ተመራጭ ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በጥሩ ሁኔታ መያዙን ገልጸዋል።

እስከታችኛው ማህበረሰብ ዘንግ ግንዛቤው እንዲኖር የሲቪክ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተበባሪ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው መካተት አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦችና በቀጣይ ማህበራቱ በትኩረት መስራት አለብን ያሏቸው ጉዳዮችን አንስተዋል።

በማኑዋሉ አካል ጉዳተኞችንና ተፈናቃዮችን በተመለከተ ለያይቶ ማስቀመጥ እንዳለበት ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ማኑዋል ረቂቅ ቋንቋን ታሳቢ እንዲያደርግ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

የተነሱ ሃሳቦችን በቀጣይ ለማኑዋሉ በግብአትነት እንደሚውሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምርጫ እስኪደርስ ድረስ ሳይጠበቅ ማንኛውም የሲቪክ ማህበረሰብ በምርጫ ወቅት ለሚሰጡት ትምህርት ከወዲሁ እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

ማኑዋሉን ማስተዋወቅ ያስፈለገውም ዝግጅት እንዲጀምሩ ለማመላከት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምርጫው የተሳካ እንዲሆንም የሲቪክ ማህበራት የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እንዲያደርጉ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።

ማኑዋሉን ለሁሉም ማህበረሰብ ከሚያደርሱ ተቋማት ውስጥ ሲቪክ ማህበራት መሆናቸውን ገልጸው በትክክል መድረሱን ደግሞ ምርጫ ቦርድ እንደሚያረጋግጥ ጠቁመዋል።

ማኑዋሉ ከጸደቀ በኋላ ማህበራቱ ያላቸው አስተዋጽኦ ገለልተኛ፣ የሙያ ብቃትን የጠበቀ፣ ከማንም ፓርቲ ያልወገነ እንዲሆን መከተል ያለባቸውን አሰራር በተመለከተ ምርጫ ቦርድ መመሪያ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም