የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድርን ወላይታ ድቻ 18ኛ ሙገር ሲሚንቶ 19ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድርን ወላይታ ድቻ 18ኛ ሙገር ሲሚንቶ 19ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2011 በግብጽ ካይሮ ከመጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ባለው 38ኛው የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ወላይታ ድቻ 18ኛ ሙገር ሲሚንቶ 19ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀቁ።
በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ሁለቱ የኢትዮጵያ የቮሊቦል ክለቦች ዛሬ በስምንተኛ ቀኑ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ወላይታ ድቻ ከማዳጋስካሩ ጌንዳርማሪ ጋር 17ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ባደረገው ጨዋታ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ሙገር ሲሚንቶ 19ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቪኤስ ምዋንጋዛ ባደረገው ጨዋታ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ትናንት ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ከ17ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በአል አህሊ የቮሊቦል ጂምናዚየም ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ወላይታ ድቻ በውድድሩ ሙገር ሲሚንቶን ጨምሮ የዴሞክራቲክ ኮንጎውን አርዲ ኤስፖይርንና የቡሩንዲውን ሩኪንዞን ማሸነፍ ችሏል።
የዴሞክራቲክ ኮንጎውን አርዲ ኤስፖይርን ያሸነፈበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ተሳትፎው ታሪክ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበበት ነበር።
ሙገር ሲሚንቶ የዛሬውን ጨምሮ በውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን ከዚህ በፊት የጊኒውን ኤኤስ ፋግን ማሸነፉ ይታወሳል። ሙገር ሲሚንቶ የጊኒውን ኤኤስ ፋግን ያሸነፈበት ውጤት በውድድሩ ተሳትፎ ታሪክ ያስመዘገበው የመጀመሪያ ድሉ ነበር።
ሙገር ሲሚንቶ በአጠቃላይ ውድድሩ በወላይታ ድቻ፣ በግብጹ አል አህሊ፣ በሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ፣ በቦትስዋናው ፖሊስ ቪአይና በኮትዲቭዋሩ ኤኤስ ኢንጄስ ተሸንፏል።
ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ያደረጉት ተሳትፎ በመድረኩ የኢትዮጵያ ስም በቮሊቦል እንዲጠራ ያደረገና ወደፊት ስፖርቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስራዎች ከተሰሩ የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ መድረክ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አመላክቷል።
የግብጹ አል አህሊና ስሞሃ ክለቦች የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር አሸናፊ ለመሆን ከቀኑ 11 ሰአት ላይ በአል አህሊ የቮሊቦል ጅምናዚየም ነገ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባለፈው ዓመት በግብጽ ካይሮ በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የአገሪቷ ክለብ አል አህሊ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።
የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1987 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አል አህሊ 13 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን 6 ጊዜ እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ 5 ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።