ቀጥታ፡

የህግ የበላይነትን ለማክበርና ለማስከበር ዝግጁ መሆናቸውን በባሌ ዞን ስልጠና የወሰዱ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት ገለጹ

ጎባ ሚያዝያ 1/2011 የህግ የበላይነትን ለማክበርና ለማስከበር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ባሌ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ስልጠና የወሰዱ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት ገለጹ፡፡

በአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ዙሪያ የሰለጠኑ 664 የሚሊሻ አባላት ተመርቀዋል፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ አብዱራሂም አህመድ በሰጡት አስተያየት " የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ያገኙት መሰረታዊ ስልጠና ያግዘናል " ብለዋል፡፡

በአካባቢው ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰተውን ግጭት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የወሰዱት ስልጠና እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

የወንጀል መንስኤዎችን ቀድሞ በመለየትና በማክሸፍ ከህዝቡ ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወሰዱት ስልጠና ስንቅ እንደሚሆናቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው ተመራቂ  አቶ አብዲሳ ከተማ ናቸው፡፡

የህግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር የተጣለባቸውን የህዝብን አደራ በመወጣት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂዎቹ  ገልጸዋል፡፡

የባሌ ዞን የፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው ተማራቂዎቹ  የህግ የበላይነትን በማክበርና ለማስከበር ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለ40 ቀናት በአካባቢ ደህንነት አጠባበቅ፣  በፀጥታ አከባበርና በህግ የበላይነት ለይ ያተኩሩ በተግባር የተደገፋ ስልጠና መከታተላቸውን አስታውቀዋል፡፡

"ተመራቂዎቹ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ፈጥረው በመንቀሳቀስ የአካባቢውን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት እንዲጠብቁ ያግዛሉ" ብለዋል።

በምረቃው ስነስርዓት የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ እንዳሉት የአካባቢውን ብሎም የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የህዝብን አደራ ተሸክሞ በቁርጠኝነት ተግቶ የሚሰራ የፀጥታ አባላት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም የፀጥታ ኃይሉን አቅም በመገንባት በራሱ የሚተማመን፣ ህዝባዊነትን የተላበሰና ሳይንሱን ቀድሞ የተረዳ የፀጥታ ኃይል ለመገንባት በቀጣይ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የፀጥታ አካላትም በአካባቢው እየተስተዋለ ያለውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመስራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም  አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም