በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ትራምፕ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ትራምፕ አቀረቡ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2011 በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳረጋገጡት፤ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የሹመት ደብዳቤያቸውን ትናንት በኋይት ሀውስ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ለፕሬዚዳንቱ አቅርበዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በባለ ራዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ታሪካዊና ሁሉን አቀፍ ለውጥ አገሪቷ በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና ዳግም ያረጋገጠችበት ነው።" ማለታቸውን አምባሳደር ፍጹም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ አጀንዳ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና ለዚህም ከአምባሳደር ፍጹም ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ወደ ዋሺንግተን እንኳን ደህና መጡ የሚል የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነትና ወዳጅነት ለማጠናከር በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በአምባሳደርነት ቆይታቸውም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል በዋንኛነት በኢኮኖሚያዊ እድገትና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
አምባሳደር ፍጹም አረጋ መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለአሜሪካ ዋና የፕሮቶኮል ኃላፊ አምባሳደር ሲን ፒ ሎውለር ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1903 ነው።
እ.አ.አ በ1903 የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አፄ ምንሊክና በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቲዮዶር ሩዝቬልት የዲፕሎማሲ ተወካይ ሮበርት ፔት ስኪነር ጋር አገሮቹ ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስምምነትም መፈራረማቸው ይታወሳል።
ሁለቱም አገሮች በተመሳሳይ እ.አ.አ 1949 ኤምባሲያቸውን በመክፈት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያና አሜሪካ በጤና፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና በትምህርት እንዲሁም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ጠንካራ የሆነ ትብብር አላቸው።
የአሜሪካ ተራድኦ (ዩኤስኤይዲ) ከተቋቋመት እ.አ.አ ከ1961 ጀምሮ በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን በድርጅቱ የሚደረገው ድጋፍ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ዋና ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።