ቀጥታ፡

ህዝብን በማሳተፍ በተከናወነው የግብርና ተፋሰስ ልማት 12 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኃብት ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2011 በተያዘው ዓመት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ህዝብን በማሳተፍ በተከናወነው የግብርና ተፋሰስ ልማት 12 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኃብት ማዳን መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የተፋሰስ ልማቱ ገንዘብ ከማዳን ባሻገር በየአካባቢው ያለውን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል የሚያስችል ሁኔታን ፈጥሯል ነው የተባለው።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ሁመር ሁሴን የበጀት ዓመቱን ያለፉ 8 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተጠቀሰው ወቅት የህዝቡን ነፃ ጉልበት በመጠቀም 1 ነጥብ 37 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የስነ አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነዋል፤ በዚህም ከ6 መቶ 69 ሺህ በላይ ተፋሰሶችን ማልማት ተችሏል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጉዳት የደረሰበት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተከልሎ እንዲያገግም የተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በተፈሰስ ልማት መርሃ ግብሩ 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ተሳትፏል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት አርሶ አደሩ የገቢያ መር የሆነ የአመራረት ዘዴን በመከተል ከገቢያ ተጠቃሚ እንዲሆን ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ በቂ ምርት እንዲያቀርብና ለኤክስፖርት ምርታችን ማሳደግ እንዲቻል የኩታ ገጠም እርሻ በ181 ወረዳዎች ተከናውነዋል።

"በዚህም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ተገኝቷል ከበቆሎ ምርት 20 በመቶ፣ከጤፍ 20 ነጥብ 7 በመቶ፣ከስንዴ 26 ነጥብ 8 በመቶ፣እና ከገብስ 22 ነጥብ 7 ዕድገት አሳይቷል" ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለማዳበሪያና ለተለያዩ ኬሚካሎች የ20 ቢሊዮን ብር ግዥ ለመፈፀም ታቅዶ ሙሉ በሙሉ መሳካቱንም ተናግረዋል።

ከክሎች በተሰበሰበ ፍላጎት መሰረት የግዥ ዕቅዱ 1 ነጥብ 27 ሚሊዮን ቶን መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዑመር ባለፉት 8 ወራት የ1 ነጥብ 12 ሚሊየን ቶን ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ይህም ከዕቅዱ 88 በመቶ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ ግማሸ ያህሉ ወደ አገር ውሰጥ የተጓጓዘ ሲሆን ቀሪው እስከ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓም ይገባል ብለዋል።

የማዳበሪያ ፍላጎትን በአገር ውስጥ በማምረት ለሟሟላት የተጀመረውን ጥረት የጠቀሱት ሚኒስትሩ  በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ኦሲፒ ከተባለው የሞሮኮ መንግስት ኩባኒያ ጋር በሽርክና በድሬደዋ የሚቋቋመውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ሥራ የማስጀመር ሂደት በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም አንስተዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦትን በሚመለከት ለዚህ ዓመት የታቀደው 2 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ የታቀደ መሆኑን አቶ ኡመር ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ 8 ወራት ውስጥ በተደረገ ጥረት የተዘጋጀው ምርጥ ዘር ግማሽ ያህሉ ሲሆን ይህም በጸጥታ ችግር በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ለማባዛት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

በዚሁ ምርት ዘመን ከተለያዩ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የግል ኩባንያዎች የቀረቡ 147 የአትክልት ዝርያዎች የተለያዩ ናሙናዎች በላቦራቶሪ ጥራት ፍተሻ ተደርጎባቸው ለሚመለከታቸው ተቋማት መላኩንም ገልጸዋል።

አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ረገድ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራትም ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም