ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በስዊዝ ፌዴራል ምክር ቤት መካከል የተፈረመውን መደበኛ የአየር አገልግሎት ስምምነት አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በስዊዝ ፌዴራል ምክር ቤት መካከል የተፈረመውን በመርሐ-ግብር የሚከናወን መደበኛ አየር አገልግሎቶች ስምምነት አዋጅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 32ኛ መደበኛ ስብሰባ የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደርና የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆችንም መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ልኳል።

በኢትዮጵያና በስዊዝ ፌዴራል ምክር ቤት መካከል የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት አዋጅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክርና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን የሚያሳድግ ነውም ተብሏል።

አዋጁ የአገሪቷን ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም ፍሰትና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የሚያጎለብት እንዲሁም የአየር መንገዶችና የበረራ አድማሱን የሚያሰፋ ነው።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ መድረስ የምትፈልግበትን ግብ ለማሳካትም ያግዛል ተብሏል።

በዚህ መሠረት ምክር ቤቱ በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር አገልግሎቶች ስምምነት አዋጅ ቁጥር 1139/2011 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

በተጨማሪም የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደር እና ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ለተፈጥሮ ሐብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ልኳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም