የስዊዲን መንግስት በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል - የአገሪቱ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የስዊዲን መንግስት በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል - የአገሪቱ አምባሳደር
አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2011 በኢትዮጵያ የሰብአዊና ፖለቲካ መብቶችን በማስጠበቅ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነትን ለማሳደግ የሚደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ የስዊዲን መንግስት አስታወቀ።
የአገሪቱ አምባሳደር ይህንን የገለፁት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ህግ ማሻሻያ ተግባራት ላይ በሚነጋገረውና ጋዜጠኞችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ዛሬ ሲጀመር ነው።
"የጋዜጠኝነት ዴሞክራሲን ማበረታታት ለሚዲያ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አደራሽ በተጀመረው አውደ ጥናት ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካና ከሲዊዲን የመጡ በሕግ እና በሚዲያ የዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀርባሉ።
አውደ ጥናቱን በዋና አጋርነት ያዘጋጀው የሲዊድን መንግሥት የኢትዮጵያ አምባሳደር ቶርጆን ፒተርሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሃሳብን በነፃነት ለመግለጽ አሳሪ የሆኑትን የአገሪቱ ሕጎች ለማሻሻል እና የዴሞክራሲ ሽግግሩን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት መንግስታቸው የሚሰጠውን ድጋፍ ይቀጥላል።
"አሁን ያለው ፈጣን ለውጥ እንዲቀጥልና በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲሄድ የሲዊዲን መንግሥት እገዛ ያደርጋል" ያሉት አምባሳደሩ፤ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው አውደ ጥናት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅን ለማሻሻል መንግሥት ያቋቋመው የባለሙያ ኮሚቴ በቂ ግብዓት ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሥር የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕጉ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ በዚሁ ምክር ቤት ሥር የመገናኛ ብዙሃን ሕግ ባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙን ጠቁመዋል።
የባለሙያ ቡድኑ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የሚገናኙ የሕግ ማዕቀፎችን የመመርመር ሥራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም ዶክተር ጌዲዮን ገልጸዋል።
አውደ ጥናቱም ለሚካሄደው የሕግ ማሻሻያ በነፃነት ግብዓቶችን ለመስጠት ጠቃሚ ውይይት እንደሚደረግ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።