ቀጥታ፡

በሰሜን ተራሮች ፓርክ ዳግም የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ

ጎንደር ሚያዚያ 1/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ዳግም የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የፓርኩ ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ አዛናው ከፍያለው ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሳት ቃጠሎው ትናንት ምሽት አካባቢ የተቀሰቀሰው በፓርኩ ግጭ በተባለው የቱሪስቶች ካምፕ አካባቢ ነው፡፡

የፓርኩ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው የጓሳ ሳር ላይ የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ከደባርቅ ከተማ የተውጣጡ የፖሊስና የልዩ ኃይል አባላት ወደ ሥፍራው ተልከው ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

''ዳግም የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት በውል አልታወቀም'' ያሉት አቶ አዛናው፣ቃጠሎው አድማሱን እንዳያሰፋ ተጨማሪ የሰው ኃይል ወደ ቃጠሎው ሥፍራ ለመላክ ጥረት በመደረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡

ሳንቃ በርና እሜት ጎጎ በተባሉት የፓርኩ አካባቢዎች ላለፉት ሁለት ሳምንታት በዘለቀው ቃጠሎ 340 ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት መውደሙና እሳቱንም መቆጣጠር ተችሎ ነበር፡፡

በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ መገኛ ሥፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም