ቀጥታ፡

ፓርኩ የአደጋ ዝርዝር ውስጥ የሚያስገባ ስጋት አልተጋረጠበትም

አዲስ አበባ ሚያዚያ 1/8/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ፓርኩ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የአደጋ መዝገብ ይሰፍራል የሚል ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ 28 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች።

ከእነዚህም መካከል እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1978 በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አንዱ ነው።

ይሁንና በአንድ ወቅት በአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ በመጡ ሕገ-ወጥ ሰፈራዎች፣ የሞፈር ዘመት የእርሻና ልቅ ግጦሽ ህልውናው አደጋ ውስጥ ወድቆ በመቆየቱ ዩኔስኮ ለ21 ዓመታት ያህል ፓርኩን በአደጋ መዝገብ ውስጥ አስፍሮ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግለት ማድረጉ ይታወቃል።

በዚህም ዩኔስኮ የተሰሩ ስራዎችን በተጨባጭ በመገንዘብ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል።

ይሁንና ከአንድ ወር በፊት በፓርኩ ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ዩኔስኮ አደጋ መዝገብ ላይ በድጋሚ እንዲገባ የሚያሰጋ አለመሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

በአጠቃላይ ወደ 412 ኪሎ ሜትር ስኩየር እንደሚሸፍን የሚነገርለት ፓርኩ በቅርቡ በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ 342 ነጥብ 9 ሄክታር የሚሆነው ክፍል ብቻ እንደተጎዳ ተገልጿል። 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፤ በተለያየ መንገድ በፓርኮች ላይ የእሳት ቃጠሎ ሊያጋጥም እንደሚችል ይታመናል።

በቅርቡም በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ በግለሰቦች የግል ጥቅም ላይ ተመስርቶ አዲስ ሳር ለማብቀልና አዲስ ማሳ ለማዘጋጀት፣ ማር ለማምረት፣ ከሰል ለማክሰል እንዲሁም የወርቅ ማእድን ለማግኘት የእሳት ቃጠሎው እንዲፈጠር ተደርጓል ብለዋል።

ይሁንና በፓርኩ ላይ የደረሰው ቃጠሎ ፓርኩ ዳግም በዩኔስኮ አደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ የሚያሰጋ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

አሁን ላይም በፓርኩ ቃጠሎ ላይ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማወቅም ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም