ቀጥታ፡

ቤተ ቤተክርስቲያኗ ለምዕራብ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና እየሰጠች ነው

ነቀምቴ ሚያዝያ 1/2011 የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ  ለምዕራብ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና  እየሰጠች ነው።

የቤተ ቤተክርስቲያኗ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ማዕከል ሲኖዶስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ቄስ ተሰማ ኤጀታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ለ10 ቀናት የሚቆየው አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖችን ለመርዳት ነው።

በነቀምቴ የዓይን ሕክምና ክሊኒክ በሚሰጠው አገልግሎት አንድ ሺህ ሰዎች ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑና ከነዚህም 400 የሚሆኑት የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና እንደሚከናወንላቸው አስታውቀዋል።

በዚህም ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና የሚደረግ ሲሆን፣ ለግላኮማ በሽተኞች ነፃ የመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ።

አገልግሎቱ በስድስት የውጭና የአገር ውስጥ ሐኪሞች እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ በምዕራብ ኦሮሚያ በተቋቋሙ ሰባት ማዕከላት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራች መሆኗንም አመልክተዋል።

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በጅማ ዞን የሊሙ ሰቃ ወረዳ የማነሳ ኤጀርሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደጀነ ስርና በሰጡት አስተያየት በአገልግሎቱ የተፈወሱ ሰዎችን አይተው በመጡበት አገልግሎት ረክቻለሁ ብለዋል።

አገልግሎቱ ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የተሻለ መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ የታዘዛላቸው መነጽር ዋጋም ተመጣጣኝ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው አቶ ወጋሪ ቀልበሳ በሰጡት አስተያየት ቤተክርስቲያኗ በተመጣጣኝ ዋጋ፣ዕውቀትና ልምድ ባላቸው ሐኪሞች በምትሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ተራ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ እስከ ሚያዝያ 9/2011 ይሰጣል።

ቤተክርስቲያኗ በጤና፣በድህነት ቅነሳ፣ሴቶችን በማብቃትና የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል መስኮች እየሰራች መሆኗንም ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም