ቀጥታ፡

በሐረር ከተማ ህገ ወጥ ናቸው የተባሉ 1ሺህ 348 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሀረር ሚያዚያ 1/2011 የሐረሪ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በከተማው በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ አግኝቻቸዋለሁ ያላቸው 1ሺ 348  የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ፡፡

በባለስልጣኑ የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አብዱላዚዝ ሱፍያን ለኢዜአ እንደገለጹት እርምጃው የተወሰደው  ከሁሉም የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የታክስ ግብረ ኃይል በማቋቋም ነው፡፡

በዚህም በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ምክንያቶች በግብር አሰባሰቡ ላይ ክፍተት እንዳለ ማየት ተችሏል፡፡

በስድስት ወሩ  579 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከንውኑ ግዴታቸውን ከተወጡ  ግብር ከፋዮች 276 ሚሊየን ብር የተገኘ መሆኑን  አቶ አብዱላዚዝ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ካለው ግብር ከፋይ  መካከል 38 በመቶው  ግዴታውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ገቢው ሊቀንስ ችሏል፡፡

ክፍተቱን ለማስተካከል ግብረ ኃይሉ ለ20 ቀናት ባደረገው እንቅስቃሴ  በከተማው ስድስቱም ወረዳዎች   ግብር ሳይከፍሉ ሲነግዱ  የተገኙ 1ሺ 348  የንግድ ተቋማት ታሽገዋል።

ከነዚህም መካከል 500  አዲስ ንግድ ፍቃድ በማውጣት ወደ ግብር ከፋይነት መምጣታቸውን ያመለከቱት የስራ ሂደቱ ባለቤት  በቀሪዎቹም ላይ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ባከናወነው  ስራ ከማስታወቂያ፣ ከዓመታዊ የንግድ ትርፍና ከሌሎችም ዘርፎች ከ7 ሚሊዮን 500ሺህ ብር  በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው በገጠር ቀበሌዎች በተመሳሳይ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በከተማው በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ አሚራ ጀማል በሰጡት አስተያየት " ለዓመታት የሚጠበቅብኝን ግብር በወቅቱ እየከፈልኩኝ የንግድ ስራዬን እያከናወንኩ ነበር ዘንድሮ ግን በወቅቱ  ግብር ባለመክፈሌ ሱቄ ሊታሸግ  ችሏል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት  የተጣለባቸውን ታክስና  ቅጣት እየከፈሉ መሆኑን አመልክተው  ከቅጣት ይልቅ ባለስልጣኑ  የግንዛቤ ትምህርት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተለይ ቅሬታን የማስተናገድ  ስራዎች ላይ ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል አንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ በከተማው በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አስፋው ከበደ ናቸው፡፡

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሚራ ዩስፍ  በበኩላቸው ነጋዴው በግብር አከፋፈሉ ላይ  የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አሁንም ግብር ከፋዩ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያግዙ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ከ13ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች  እንደሚገኙም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም